በሊጉ ጨዋታዎች አራት ቡድኖች አቻ ተለያዩ

319

ሶዶ/ሽሬእንዳስላሴ ታህሳስ 22/2011 በስምንተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ እግር ኳስ ጨዋታ ወላይታ ድቻ ከድሬዳዋ ከነማ እንዲሁም ስሑል ሽሬና መቀሌ ሰብዓ እንደርታ አቻ ተለያዩ፡፡

ወላይታ ድቻ እና ድሬዳዋ ከነማ አንድ ለአንድ የተለያዩበትን ጨዋታ በዋና ዳኝነት የመሩት  የፌደራሉ መላኩ ፈንቴ ናቸው፡፡

በዚህ ጨዋታ  የመጀመሪያው ክፍለ ጊዜ በአስረኛው ደቂቃ ባለሜዳው የወላይታ ድቻ የተሻለ እንቅስቃሴ በማሳየት በ22 ቁጥሩ ጸጋዬ አበራ አማካኝነት ባስቆጠረው ጎል  መምራት ችሎ ነበር፡፡ 

ከግቧ መቆጠር በኋላ የድሬዳዋ ከነማ ቡድን ጨዋታውን ለመቆጣጠር ባደረገው ጥረት በ15ኛ ደቂቃ ላይ አስር ቁጥሩ ረመዳን ናስር የተጋጣሚውን የግብ ጠባቂ መዘናጋቱን ተጠቅሞ   አቻ ያስደረገውን ጎል ማስቆጠር ችሏል፡፡

ይሁን እንጂ ሁለቱም ቡድኖች ተጨማሪ ግብ ሳያስቆጥሩ ከዕረፍት በፊት ባስቆጠሯቸው  ግቦች አቻ ተለያይተዋል፡፡

የወላይታ ድቻ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሃ በሰጡት አስተያየት ቡድናቸው  ከሽንፈት የተመለሰ በመሆኑ በጨዋታው ላይ ያሳየው መነሳሳት መልካም ሊባል እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

” የሜዳ ዕድሉን ለመጠቀም  በሁለተኛዉ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ተጋጣሚያችንን ለማስጨነቅ ብንሞክርም አጋጣሚዎችን በአግባቡ መጠቀም አለመቻላችን ዋጋ አስከፍሎናል” ብለዋል፡፡

ቡድናቸው  እየተሻሻለ መምጣቱን የገለጹት ደግሞ  የድሬዳዋ ከነማ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ ስምኦን አባይ ናቸው፡፡

“ተጋጣሚያቸው ካለው  ጥንካሬና የቡድን ስብስብ እንዲሁም ከሜዳ ውጭ ካሳዩት ብልጫ አንጻር ማሸነፍ ይገባን ነበር “ብለዋል፡፡

ብዛት ያላቸው ተመልካቾች በሜዳው በመገኘት ስፖርታዊ ጨዋነት በተላበሰ መልኩ ቡድናቸውን አበረታትተዋል፡፡

ሆኖም ጨዋታው  ከተጠናቀቀ በኋላ በተጨዋቾች መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ተመልካች ድንጋይ ወርውሯል በሚል ምክንያት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተፈጥሮ እንደነበር መመልከቱን ሪፖርተራችን ገልጿል፡፡

የጸጥታ ኃይሉ ችግሩን ለመቆጣጠር በፈጣን አኳኋን  የተጠቀመው አስለቃሽ ጭስ አግባብነት እንደሌለውና ሊታረምም እንደሚገባም አስተያየት ሰጪዎች አመልክተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ  ስሑል ሽሬና መቀሌ ሰብዓ እንደርታ ባደረጉት ጨዋታ ያለምንም ግብ ተለያይተዋል፡፡

መቀሌ ሰብዓ እንደርታ ተጭነው ቢጫወቱም የስሑል ሽረ ተከላካዮችን ማለፍ ባለመቻላቸው  ጎል ሳያቆጥሩ ቀርተዋል።

ስሁል ሽሬዎችም ለግብ የሚሆኑ ኳሶች ቢያገኙም አጋጣሚውን  ሊጠቀሙበት ባለመቻላቸው እንዲሁ።

የመቀሌ ሰብዓ እንደርታ ዋና አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ አንድ ሽንፈትና ሁለት ተደጋጋሚ ነጥብ በመጣሉ ሽሬ ድረስ የመጡ የቡድኑ ደጋፊዎች በአስልጣኙ ላይ ቅር መሰኘታቸውን ተናግረዋል።

” ምንም እንኳን ልምድና ብቃት ካለው ክለብ ብንጫወትም ተጫዋቾቼ ያሳዩት እልህ የተሞላበት ፉክክር አደንቃለሁ ” ያሉት ደግሞ የስሑል ሽሬ የእግር ኳስ ዋና አስልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ ናቸው፡፡

ብዛት ያላቸው ተመልካቾች በሁለቱ  ሜዳዎች በመገኘት ስፖርታዊ ጨዋነት በተላበሰ መልኩ ቡድናቸውን አበረታትተዋል፡፡

በሽሬ እንዳስላሴ ስታዲዮም የተካሄደው ጨዋታ  የተከታተሉ  በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች ስፖርታዊ ጨዋነት በተላበሰ ሁኔታ ክለቦቻቸውን  አበረታትተዋል።