የህግ የበላይነትን ማስከበር ይገባል -የሚዛን አማን ነዋሪዎች

77
ሚዛን ግንቦት 17/2010 ጥፋተኞችን በመለየትና ተጠያቂ በማድረግ የህግ የበላይነትን ማስከበር እንደሚገባ የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች አመለከቱ፡፡ በከተማውና በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ ማህበረሰብ መካከል ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት ለመፍታትና አካባቢውን ወደ ቀድሞ ሰላም መመለስ በሚቻልበት ላይ ዛሬ ከንግዱ ህብረተሰብና ከሌሎች ነዋሪዎች ጋር ውይይት ተካሄዷል፡፡ የውይይቱ ተሳታፊዎች በወቅቱ ተፈጥሮ የነበረው ረብሽ  ምንጭና ጥፋተኞቹ ተለይተው ህጋዊ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት አመልክተዋል፡፡ የከተማዋ ነዋሪ አቶ ንጉሴ ሃብቴ በውይይቱ ወቅት "  ጥፋተኞች አስተማሪ የሆነና ተመጣጣኝ ቅጣት ሊያገኙ "ይገባል ብለዋል፡፡ በቀጣይም ተመሳሳይ ግጭት እንዳይደገም የግጭት ምክንያቶችን ከምንጫቸው ማደረቅ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡ ጥፋተኞችን በማጋለጥም ሆነ የከተማዋን ሰላም በማስጠበቅ ረገድ ከመንግስት ጎን በመሆን የድርሻቸውን እንደሚወጡም  ገልጸዋል፡፡ በከተማው በንግድ ስራ የተሰማሩት አቶ ምኞት ሰለሞን በበኩላቸው "በረብሻው ወቅት ባጋጠመው የንብረት ዘረፋ የህግ አካላት ድርጊቱ በማስቆም ረገድ ሚናቸው ዝቅተኛ ነበር "ብለዋል፡፡ "ሰላምና ደህንነት በሌለበት ሁኔታ እድገት አይታሰብም "ያሉት አቶ ምኞት በቀጣይም መንግስት ሰላሙን በማረጋገጥ ረገድ ትኩረት ሰጥቶ መስራት አንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ የግብይት ስራቸውም ለቀናት  በመስተጓጎሉም  መጎደታቸውን ያመለከቱት አስተያየት ሰጪው ሰላም ከሌለ ስራቸውን ማከናወን እንደማይችሉ መገንዘባቸው ተናግረዋል፡፡ የከተማዋን ሰላም ለመመለስ በሚደረገው ጥረት እሳቸውን ጨምሮ የከተማዋ ነዋሪ ሚና ከፍተኛ መሆን እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ ረብሻው ገና ከዩኒቨርሲቲው ማስቆም ይቻል እንደነበርና ይህ ባለመሆኑ በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የገለጹት ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ሙሉጌታ ተስፋዬ ናቸው፡፡ መንግስት በንብረታቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸውን ግለሰቦች አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርግላቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ "ከተማዋን ወደ ቀደመ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለመመለስ ሁላችንም የበኩላችንን መወጣት ይገባናል፤ጥፋተኞችን የማጋለጥና የህግ የበላይነትን ማስከበር ይገባል "ብለዋል፡፡ የቤንች ማጂ ዞን  ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወንድሙ ገብሬ በበኩላቸው ተፈጥሮ በነበረው ረብሻ በደረሰው የንብረት ውድመት ማዘናቸውን ገልጸው ጥፋተኛችን ለይቶ ለመያዝ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ "እስካሁንም ከ100 በላይ ተጠርጣሪዎች በህብረተሰቡ ጥቆማና በጸጥታ ሃይሉ ትብብር በቁጥጥር ስር ውሏል "ብለዋል፡፡ ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማም በርካታ የግለሰብ ንብረቶችን ተመላሽ መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲውም ሆነ በከተማው  ተከስቱ በነበረው ረብሻ  ተሳታፊ የነበሩ ግለሰቦችን በማጣራት ሂደት ህብረተሰቡ ተባባሪ እንዲሆንም ጠይቀዋል፡፡ በውይይት መድረኩ የተገኙት በሚኒስትር ማዕረግ የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ የምርምር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ጸጋዬ ማሞ  " የከተማዋን እንቅስቃሴ ወደ ቀደመ ሰላሟ መመለስ ቀዳሚ ተግባር ነው" ብለዋል፡፡ "ክስተቱ ህብረተሰቡን የማይገልጽ ነው " ያሉት አቶ ጸጋዬ የችግሩን ምንጭ መንግስት እንደሚለየውና ባጠፉትም  ላይ ተገቢውን እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል፡፡ የከተማዋን ሰላም በመመለስ ሂደት ህብረተሰቡ ተሳትፎውን ማጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ውይይት በተለያዩ መዋቅሮች እንደሚቀጥልና በከተማዋ ያሉ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ወደ ቀደመ ስራቸው እንዲመለሱ ከከተማው ነዋሪ ጋር ከስምምነት ተደርሷል፡፡ በከተማውና በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ ተፈጥሮ የነበረው ረብሻና  ችግሩ ለመፍታት ሲደረግ የቆየውን  ጥረት  ኢዜአ በተከታታይ መዘገቡ ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም