ወጣቱ በአገራዊ ራዕይ ላይ እንዲያተኩር ተጠየቀ

129

ሰመራ ታህሳስ 21/2011 ወጣቱ ከጎጠኝነትና ከጎሰኝነት አጀንዳዎች ይልቅ በአገራዊ ራዕይ ላይ ማተኮር እንደሚገባው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ኡባንግ ሜቶ አሳሰቡ።

አቶ ኦባንግ ትናንት ከሰመራ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጋር ባካሄዱት ውይይት እንደተናገሩት ወጣቱ ባለፉት 27 ዓመታት በልዩነቶች ላይ  ያተኮረው አመራር ይከተለው ከነበረው ከፋፋይ ፖሊሲ በመውጣት አገራዊ እሴቶችን አውቆ ወደሚተገብርበት ሁኔታ መሸጋገር አለበት።

ከራስ ጥቅምና መብት እኩል ስለሌሎች ብሄርና እምነት ተከታዮች ብሎም አገራቸው ሰላሟ ተረጋግጦ  በሚኖሩበት  ሁኔታ ላይ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የጋራ አገሩን ለመገንባትና ለአንድነቷ በመታገል ራዕይዋን ለማሳካት መሥራት እንዳለበትም ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት ዜጎች ለዘመናት የገነቧቸዉ ተከባብረው የመኖር አኩሪ እሴቶች መሸርሸራቸውን ገልጸው፣ይህም አለመተማመንና አንዱ ሌላውን በጥርጣሬና በስጋት እስከማየት የደረሰበት ሁኔታ መፈጠሩን አስታውሰዋል።

በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ  ግጭቶች ባለፉት የዘር ተኮር ፖለቲካ  ድምር ውጤቶች ናቸው ያሉት አቶ ኦባንግ፣አሁኑኑ እልባት ካላበጀንላቸው የአገሪቱን ህልውና የሚያጠፉ ተጨባጭ ማሳያዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአገሪቱ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ እንዲደናቀፍ ሀብታቸውን፤ እውቀታቸውንና አደረጃጀታቸውን ተጠቅመው አገርንና ሕዝብን በማተራመስ  የተጠመዱ አካላትን ወጣቱ ነቅቶ ሌላውንም ኅብረተሰብ የማንቃት አገራዊ ኃላፊነት እንዳለበትም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ተናግረዋል።

በመሆኑም ወጣቱ በሚያጋጥሙት ጥቃቅን ችግሮች  ሳቢያ በስሜታዊነት ወደግጭት በመግባት የሴራ ፖለቲከኞች መጠቀሚያ እንዳይሆን በሰከነ መንገድ መንቀሳቀስ እንዲሁም በግልጽ መነጋገርና መወያየት መጀመር አለበት ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲዉ የአራተኛ ዓመት ምህንድስና ተማሪ  መሐመድ ኢድሪስ ወጣቱ አገራዊ ኃላፊነቱን ዘንግቶ ባልተረጋገጠ መረጃ በስሜት ተነስቶ ወደ ግጭት የሚገባበት ሁኔታን እንዲቀይር ጠይቋል።

ከማናቸውም አካላት የሚደርሱትን መረጃዎች በማጣራት እውነትም ከሆነ በስሜት ሳይሆን በሰከነ መንገድ በውይይት መፍታት ያስፈልጋል ብሏል።

ሌላው የዩኒቨርሲቲዉ የአራተኛ ዓመት ምህንድስና ተማሪ ጌታነህ ተስፋው በማህበራዊ ሚዲያም  ሆነ አክቲቪስቶች የሚያሰራጯቸውን ሚዛናዊነት የጎደላቸዉ መረጃ አጥርቶ መጠቀም እንደሚያስፈልግ አመልክቶ፣መረጃውን የሚያስተላልፉ ተቋማት ላይ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባም አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም