የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አዳዲስ ሹመቶችን ሰጠ

67

አሶሳ ታህሳስ 20/2011  የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አዲስ አፈ-ጉባኤ እና ምክትል አፈ-ጉባኤ ሲመርጥ ከአሶሳ ከተማ ግጭት ጋር በተያያዘ የተጠረጠረ አንድ የምክር ቤት አባል ያለመከሰስ መብት አንስቷል፡፡

ምክር ቤቱ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ባካሄደው ሶስተኛ አስቸኳይ ጉባኤው መልቀቂያ ባቀረቡት የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤዎች ምትክ አቶ ሃብታሙ ታዬ በዋና አፈ-ጉባኤነት አቶ ኢሳቅ አብዱልቃድርን ደግሞ በምክትል አፈ-ጉባኤነት ሾሟል፡፡

18 የነበሩ የክልሉ አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶችንም ወደ 14 አውርዷል፡፡

ከእነዚህ መካከል አንዱ ከዚህ ቀደም ፍትህ ቢሮ ተብሎ ሲጠራ የነበረውና አሁን በአዲስ መልክ የክልሉ ጠቅላይ አቃቢ ህግ ተብሎ እንዲደራጅ የተደረገው አንዱ ነው፡፡

እስከ ወረዳ ድረስ አደረጃጀት እንደሚኖረው የተገለጸ ሲሆን ተጠሪነቱም በየደረጃው ለሚገኙ መስተዳደሮች እንደሚሆን ተመልክቷል፡፡

ከምክር ቤት አባላት መካከል አቶ ደስታየሁ ምት እንደተናገሩት የህብረተሰቡን ፍላጎት መሠረት አድርጎ ተቋማትን መልሶ ማደራጀቱ ተገቢ እደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

ይሁንና ተቋማትን በአዲስ መልክ ማደራጀትና ማጠፍ በመሠረታዊ ጥናት ላይ ካልተመረኮዘ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም ግብርና ቢሮ፣ ተፈጥሮ ሃብት እና ምግብ ዋስትና አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ቢሮዎች ግብርና ቢሮ በሚል መዋቀሩን ጠቅሰው ተቋማቱ ተመጋጋቢ ቢሆኑም በአፈጻጸም ወቅት ችግር ሊያጋጥም እንደሚችል ጠቁመዋል።

አቶ በላይ ወድሻ የተባሉ የምክር ቤት አባል ደግሞ ከክልል ጀምሮ በየደረጃው የሚዋቀረው የጠቅላይ አቃቢ ህግ መዋቅር ተጠሪነቱ ለቅርብ መስተዳድሮች መሆኑ ገለልተኛነታቸውን ጥያቄ ውስጥ ያስገባል የሚል እምነት እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ቢሮ የለውጥ እና መልካም አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ፊሊጶስ እንዳሉት ተቋማቱ በአዲስ መልክ የተዋቀሩት የተግባር እና የሃላፊነት መደበላለቅ እንደታየባቸው በጥናት በመረጋጡ ነው።

“አዲሱ አደረጃጀት የተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ በማቀላጠፍ ለህብረተሰብ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በሚያስችል መልኩ ተደራጅቷል” ብለዋል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ ባላፈው ሰኔ በአሶሳ ከተማ በተከሰተው ግጭት ከሞቱ 15 ሰዎች ጋር በተያየዘ ጠርጥሮ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት የምክር ቤቱ የአቶ ባበክር ከሊፋን ያለመከሰስ መብት አንስቷል፡፡

“በህግ የበላይነት መከበር አምናለሁ ” የሚሉት አቶ መሃመድ አብዱላዚዝ የተባሉ የምክር ቤት አባል ያለመከሰስ መብቱ መነሳቱን ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

በህግ በምትመራ ሀገር ነው የምንኖረው በሚል ለምክር ቤቱ አባላት ማብራሪያ የሰጡት የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን ለህግ የበላይነት መከበር ሲባል የምክር ቤቱ አባል ያለመከሰስ መብቱ መነሳቱ ተገቢነቱን አስረድተዋል፡፡

“እውነታውን በትክክል ማሳወቅ ጉዳዩን ከያዘው የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ ይጠበቃል” ብለዋል ።

ምክር ቤቱ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቅራቢነት የ12 ካቢኔ አባላት ሹመት በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡

በዚሁ መሠረት አቶ አድጎ አምሳያ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድ ፣አቶ አበራ ባዬታ የክልሉ ሠላም ግንባታ ጸጥታ ቢሮ ፣ አቶ ሙሳ አህመድ የግብርና ቢሮ ፣ አቶ ዚያድ አብዱላሂ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ፣ ወይዘሮ ፍሬሕይወት አበበ ጤና ቢሮ ፣ አቶ ኢብራሂም ኡመር የክልሉ ጠቅላይ አቃቢ ህግ ዋና አቃቢ ህግ፣ አቶ አሰር ኢብራሂም የኢንቨስትመንት አካባቢ መሬት አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ አድርጎ ሾሟል።

እንዲሁም አቶ ቀልቤሳ ኦልጅራ የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ፣ አቶ አካሻ እስማኤል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ፣ አቶ ጸጋዬ ተሰማ ውሃ መስኖና ኢነርጂ ቢሮ፣ ወይዘሮ ጸሐይ ሞርካ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ ወይዘሮ ሂጅራ ኢብራሂም ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ቢሮ ሃላፊ ሆነው ተሹመዋል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት የክልሉ ዋናው ኦዲተር የነበሩት ወይዘሮ ጸሃይ ሞርካን የመልቀቂያ ጥያቄ ተቀብሎ በምትኩ አቶ ከማል ሃሰንን ዋና ኦዶተር አድርጎ ሾሟል፡፡

አዲስ የተሾሙት ሁለቱ የምክር ቤት አፈ-ጉባኤዎች የተሰጣቸውን ሃላፊነት በሚገባ ለመወጣት ቃል የገቡ ሲሆን የህብረተሰቡንና የምክር ቤቱን አባላት እገዛ ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም