ለውጡ የተፈለገውን ውጤት እንዲያስገኝ የሁሉንም ተሳትፎ ይሻል--አቶ ኦባንግ ሜቶ

46

ሰመራ ታህሳስ 20/2011 የተጀመረው የለውጥ ጉዞ የሚፈለገው ደረጃ ላይ እንዲደርስ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል የድርሻውን እንዲወጣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ኦባንግ ሜቶ ጠየቁ።

አቶ ኡባንግ ከሰመራ ዩንቨርሲቲ ማሀብረሰብ አባላት ጋር በሀገራዊ ለውጡና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ  ውይይት እድርገዋል።

በውይይቱ ላይ አቶ ኡባንግ እንደገለጹት በሀገራችን በተለያዩ ግዜያት በህዝቦች የህይወት መስዋዕትነት የተጀመሩ አብዮቶች በተደራጀ አግባብ ባለመመራታቸው የሚፈለገውን ውጤት ሳያመጡ ዋጋ አስከፍለዋል።

በመሆኑም ካለፉት ስህተቶች በመማር በዶክተር አብይና አጋሮቻቸዉ በተጀመረው የለውጥ ጉዞ ህብረተሰቡ የሚፈልገው ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተረጋጋጡባት ማህበራዊ ፍትህ የሰፈነባት ሀገር ለመገንባት የሚያስችል መልካም እድሎችን መኖራቸውን አስረድተዋል

“በመሆኑም ሁሉም ህብረተሰብ ከአክራሪ ብሄርተኛነትና ተያያዥ ከፋፋይ አጀንዳዎች ርቆ ሰብአዊ ክብርንና ኢትዩጵያዊነት በማስቀደም የሀገራችንን ሰላምና አንድነት ማስቀጠል ይኖርበታል ” ብለዋል ።

“በተለይም ዩኒቨርሲቲዎች የነገ ሀገር ተረካቢ ወጣቶች አብረው የሚኖራባቸው በመሆናቸው ለሀገራዊ ለውጡ እንቅፋት ሊሆኑ ከሚችሉ የተሳሳቱ አመለካከቶች በመውጣት የተጀመረውን ለውጥ ወደፊት ለማስቀጠል ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል” ብለዋል

የሰመራ ዩንቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አደም ቦሬ እንደተናገሩት የለውጡ ጉዞ ለእውነተኛ ዴሞክራሲና ሀገራዊ አንድነታችን መረጋገጥ ወሳኝ ነው።

“በመሆኑም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ለውጡን ለመደገፍ በየጊዜው በራሱ ምሁራን ተደጋጋሚ የውይይት መድረኮችን ለዩንቨርሲቲውም ይሁን ለአካባቢው ማህበረሰብ በማዘጋጀት ሃላፊነቱን ይወጣል”ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው 4ኛ አመት ኢንጂነሪን ተማሪ መሃመድ እድሪስ በዩንቨርሲቲ ቆይታዉ ከተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች የመጡ የተለያየ አመለካከትና እምነት ተከታዮች ቢሆኑም በሰላም ተከባብሮ በመኖር ለሌሎች ተሞክሮ እንደሚሆን ተናግሯል።

ዩኒቨርሲቲዎች ለህብረተሰቡ የማህራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ተግብራት በማከናወን የቴክኖሎጂ መፍለቂያ ሊሆኑ ሲገባ የግጭት ምንጭ መሆናቸው ተገቢ አለመሆኑን ገልጿል።

የሲቪክስ አንደኛ አመት ተማሪ የሆነችው ብሌን አይተነው በበኩሏ “አቶ ኡባንግ ስለአዲሲቱ ኢትዮጵያ በየመድረኩና በየሚዲያው የሚያስተላልፉት ምክር አዘል ቁም ነገር ለአዲሱ ትዉልድ ጠቀሚታው የጉላ ነዉ”ብላለች።

በአካል ተገናኝተው የሰጡትን ምክር በዩኒቨርሲቲ ቁይታቸውም ሆነ በወደፊት ሕይወታቸው በመተግበር ለሀገራዊ ለውጡና ለሰላም እሴት ግንባታ የበኩሏን ሚና አንደምትወጣ ቃል ገብታለች። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም