ሽምብራና አኩሪ አተር ወደ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ሊገባ ነው

1586

አዳማ ታህሳስ 20/2011 የሽምብራና አኩሪ አተርን ወደ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት በማስገባት ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ምርቱን መረከብ እንደሚጀምር የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አስታወቀ።

ከኦሮሚያ ክልል  ለተወጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት የግብይት ሥርዓቱን በማስመልከት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ዛሬ በአዳማ ተካሄዷል።

በኢትዮጵያ ምርት ገበያ  የስልጠናና አቅም ግንባታ ቡድን መሪ አቶ ሰለሞን መስረሻ እንዳሉት በሽምብራና አኩሪ አተር ምርታማነት የሚታወቁ በኦሮሚያ፣ቤንሻንጉል፣አማራና ደቡብ ክልሎች የምርት መረከቢያ የግብይ ማዕከላት ተዘጋጅተዋል።

በዚህም ለሽምብራ ምርት አቅራቢዎች አዳማ፣አዲስ አበባ፣ጎንደር፣ኮምቦልቻና ቡሬ ቅርንጫፎች ለግብይት ዝግጁ ናቸው።

በተመሳሳይ ለአኩሪ አተር ምርት አቅራቢዎች አዲስ አበባ፣አሶሳ፣ፓዌ፣ቡሬ፣ነቀምትና ጎንደር በሚገኙት የምርት ገበያ ቅርንጫፎች አምራቹ ማህበረሰብ ምርቱን ማቅረብ እንደሚችል አስታውቀዋል።

በየዓመቱ ከ812ሺህ ኩንታል በላይ አኩሪ አተር   በሀገሪቱ እንደሚመረት የተናገሩት አቶ ሰለሞን 99 በመቶ አኩሪ አተርና ሽምብራን በሚያመርቱት አካባቢዎች ላይ ዘመናዊ የኤሌክትሮንክስ ግብይት እየተከፈቱ መሆናቸውን አስረድተዋል።

“ትግራይ፣ደቡብ፣ኦሮሚያ፣አማራና ሌሎች ክልሎችም በየዓመቱ 500ሺህ ኩንታል የሚጠጋ የሽምብራ በማምረት ይተወቃሉ “ብለዋል።

ቡድን መሪ እንዳሉት የሀገሪቱ  አኩሪ አተርና የሽምብራ ምርት በህንድ፣ቻይና፣ሲንጋፖር፣ቬትናም፣የተባበሩት አረብ ኢማሬትስ፣ኢራንና ፓክስታን በግንባር ቀደምትነት የሚፈለግ መሆኑን በተደረገው የገበያ ጥናት ተረጋግጧል።

የኦሮሚያ ገበያ ልማት ኤጄንሲ ኃላፊ አቶ ገመችስ መላኩ በበኩላቸው “የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ የክልሉ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች አኩሪ አተርና ሽምብራን በጥራት ለማዕከላዊ ገበያ እንዲያቀርቡ አቅም የሚፈጠር ” ነው ብለዋል።

በአብዛኛው የክልሉ ዞኖችና ወረዳዎች ሽምብራና አኩሪ አተር እንደሚመረት አመልክተው ከዚህ በፊት  ምርቱ በደላሎች አማካይነት ለነጋዴው የሚቀርብ በመሆኑ አርሶ አደሩ በሀብቱ ላይ የመደራደርና የመወሰን እድል እንዳልነበረው ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ምርቱ ወደ ዘመናዊ የግብይት ሰንሰለት በመግባቱ አርሶ አደሩ ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርገው  ከመሆኑም በሻገር በቀጣይነት የተሻሻሉ ምርጥ ዘር በመጠቀም በጥራትና በብዛት ማምራት እንደሚያስችለው ገልጸዋል።

በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ  ከ35 ወረዳዎች የተወጣጡ ከ160 በላይ የዘርፉ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።