በድሬዳዋ የተገነባው የውሀ ፕሮጀክት በከፊል አገልግሎት መስጠት ጀመረ

371

ድሬዳዋ ታህሳስ 20/2011በድሬዳዋ ከተማ አንድ ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ የተገነባው የመጠጥ ውሀ ማስፋፊያ ፕሮጀክት በከፊል አገለግሎት መስጠት መጀመሩን የከተማው ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

ፕሮጀከቱ በሶስት ሳምንት ውስጥ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተነግሯል።

የባለስለጣኑ የውሃ አቅርቦትና ስርጭት ኃላፊ አቶ ካሚል ኢብራሂም እንደገለፁት ከአለም ባንክ በብድር በተገኘና  የከተማው አስተዳደር በመደበው በጀት የተገነባው የንፁህ መጠጥ የውሀ የተቋም በከፊል አገልግሎት መስጠት ጀምሯል ።

በፕሮጀክቱ ውሀ ማመንጨት የጀመሩ የ14 ጥልቅ ጉድጓዶች ቁፋሮ፣ 4ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ የሚያጠራቅሙ የዘጠኝ ጋኖችና 95 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው የውሀ ማከፋፈያ መስመሮች ዝርጋታ ተከናውነዋል ።

የፕሮጀክቱ ቀሪ የመስመር ዝርጋታ ስራዎች  በሶስት ሳምንት ውስጥ ተጠናቆ በሙሉ አቅሙ ለአገልግሎት እንደሚበቃ አመላክተዋል ።

“ፕሮጀክቱ አሁን ያለውን የከተማውን ህዝብ የውሀ ፍላጎት 90 በመቶ በሟሟላት ለ20 ዓመታት አገልግሎት የመስጠት አቅም” አለው ብለዋል ።

በከተማው በከፊል በተጠናቀቀው የውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ ከሆኑት መካከለ የገንደ ገራዳ፣ የከዚራ፣ የጀርባ፣ የኢንዱስትሪ መንደር የጋራ መኖሪያ ቤት ነዋሪዎች ይገኙበታል፡፡

ወይዘሮ ዘሀራ ሁሴን የገንደ ገራዳ ነዋሪ ሲሆኑ  ከዚህ ቀደም ጨቅላ ህፃን ተሸክሞ ውሃ ፍለጋ መንከራተት አሰልቺና አስቸጋሪ እንደነበር አስታውሰዋል ።

“ለአንድ ባለ 20 ሊትር ጀሪካን ውሃ ለትራንስፖርትና ለተሸካሚ እስከ 15 ብር እከፍል ነበር ” ያሉት ወይዘዋ በቅርቡ የቧንቧ ውሀ ስርጭት በመጀመሩ ችግራቸው መቃለሉን ተናግረዋል ።

“አራተኛ ፎቅ ላይ ውሀ ማግኘት አይታሰብም ነበር” ያሉት ደግሞ የኢንዱስትሪ መንደር የጋራ መኖሪያ ቤት ነዋሪ ወይዘሮ አመለወርቅ ረታ  ናቸው፡፡

አሁን ላይ  ለ24 ሰዓት የውሀ ስርጭት በማግኘታቸው እፎይታ ማግኘታቸውን ገልጸዋል ።

በአንጻሩ “የአካባቢው ነዋሪ በከፍተኛ የውሃ ችግር እየተሰቃየ ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡት ደግሞ የአዲስ ከተማ የእጦጦ አካባቢ ነዋሪ ወይዘሮ አይናለም ማሞ ናቸው ።

ወይዘሮ አይናለም እንዳሉት እየተሰራ ያለውን የውሀ ተቋም ህዝቡ እንዲጎበኝ መደረጉ ነዋሪው ስርጭቱን በቅርቡ እንደሚያገኝ እምነትና ተስፋ እንዲያድረበት አድርጓል።