የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲው ቴፒ ካምፓስ በመጪው ወር ተማሪዎችን ይቀበላል

1362

ሚዛን ታህሳስ 20/2011 የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ቴፒ ካምፓስ ከጥር 3/ 2011 ዓ.ም ጀምሮ ነባርና አዲስ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር እንደሚጀምር አስታወቀ።

በዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶክተር አህመድ ሙስጠፋ ለኢዜአ እንደገለፁት በቴፒ ከተማና አካባቢው ተፈጥሮ የነበረው የጸጥታ ችግር ወደ ቀድሞ  ሰላሙ  በመመለሱ ተማሪዎችን ለመቀበል ተዘጋጅቷል ።

ከአካባቢው አስተዳደር፣ ከሚመለከታቸው የበላይ አካላትና ህብረተሰብ ጋር በተደረገው ውይይት ና የጋራ ስምምነት ከጥር 3 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለነባርና አዲስ ተማሪዎች ይቀበላል ።

“በመርሀ ግብሩ መሰረት  ጥር 3 እና 4 ነባር ተማሪዎች እንዲሁም ጥር 6 እና 7 አዲስ ገቢ ተማሪዎች  ምዝገባ ይካሄዳል ” ብለዋል ።

በቀሪው የትምህርት ዘመን የባከነውን ጊዜ ለማካካስ የዕረፍት ጊዜና ቀናትን ጨምሮ ትምህርት እንደሚሰጥ  አመላክተዋል ።

እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለፃ በዩኒቨርሲቲው የቴፒ ካምፓስ የሚሰጠው ትምህርት የተፈጥሮ፣ የኮምፒዮተርና ምህንድስና ሳይንስ ዘርፎች ነው ።

የዩኒቨርስቲው ሚዛን ካምፓስ ግን ቀደም ብሎ ትምህርት  መጀመሩን አመልክተዋል፡፡

በፀጥታ ችግር በቴፒ ከተማና አካባቢው ከአራት ወር በላይ ተቋርጠው የቆዩ የመንግስትና የግል አገልገሎት መስጪዎች ስራ መጀመራቸውን ኢዜአ ቀደም ብሎ ዘግቧል።