የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪው በእስራትና በገንዘብ ተቀጣ

58

መቱ ታህሳስ 19/2011 በኢሉአባቦር ዞን ቡሬ ወረዳ 43 ክላሽንኮቭ ጠመንጃዎችን በህገ-ወጥ መንገድ ሲያዘዋውር በቁጥጥር ስር የዋለው ግለሰብ በስድስት አመት ጽኑ እስራትና በገንዘብ  ተቀጣ፡፡

የወረዳው ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ ገነሞ ባቢሶ እንዳሉት የፍርድ ውሳኔው የተሰጠው በ13/4/2011 ዓ.ም ከጋምቤላ ወደ መሀል ሀገር የጦር መሳሪያዎቹን በማጓጓዝ ላይ በነበረ መብራቴ ጥሩነህ በተባለ ተከሳሽ ነው።

ተከሳሹ በወቅቱ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3  -92943 ኢት በሆነ ሲኖትራክ ተሸከርካሪ በጫነው አሸዋ ስር በመደበቅ ለማሳለፍ ሲሞክር በህብረተሰቡና በጸጥታ ሀይሎች በተደረገው ፍተሻ በቁጥጥር ስር መዋሉን ተናግረዋል፡፡

ግለሰቡን በቁጥጥር ስር በማዋል አቃቤ ህግ የመሰረተውን ክስ ሲመረምር የቆየው ፍርድ ቤቱ በዛሬው እለት በዋለው ችሎት ውሳኔውን አስተላልፎበታል፡፡

ግለሰቡ በአቃቤ ህግ የተመሰረተበትን ክስ መከላከል ባለመቻሉ የአቃቤ ህግን የሰነድና የሰው ማስረጃ መሰረት በማድረግ በስድስት አመት ጽኑ እስራትና በ10ሺ ብር እንዲቀጣ እንደተወሰነበትም ተናግረዋል።

በህገ-ወጥ መልኩ ሲዘዋወር የነበረው 43 ክላሽንኮቭ ጠመንጃና 43 ካርታ ጥይትም ለመንግስት ገቢ እንዲሆን ተወስኖበታል፡፡

የወረዳው አቃቤ ህግ አቶ ሁንዴ ተፈራ በበኩላቸው ህገ-ወጥ የጦር መሳርያውን በቁጥጥር ስር ለማዋል በተደረገው ጥረት  ህብረተሰቡ ላሳየው ከፍተኛ አስተዋጽዎ አመስግነዋል፡፡

በቀጣይ መሰል ወንጀሎችን ለመከላከል ህብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጎን በመቆም የተለመደውን ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር ቀደም ሲል ድርጊቱን ተከታትሎ ከስፍራው መዘገቡ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም