ሕጋዊ የጦር መሣሪያ ባለንብረቶች አጠቃቀማቸው በአግባብ እንዲሆን አሳሰበ

52

ባህር ዳር ታህሳስ 19/2011 በአማራ ክልል የጦር መሣሪያዎችን በሕጋዊ መንገድ ያስመዘገቡ ባለንብረቶች አጠቃቀማቸውን አግባብ ባለው መልክ እንዲሆን የክልሉ ሚሊሺያ ጽህፈት ቤት አስገነዘበ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ መኳንንት መልካሙ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳሳሰቡት በክልሉ ሕጋዊ የጦር መሣሪያዎችን ያስመዘገቡ ባለንብረቶች አጠቃቀማቸው ጥንቃቄ የተሞላበት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

የክልሉ ነዋሪዎች በተደጋጋሚ በሚያነሱት ጥያቄ መሠረት ፈቃድ መሰጠቱን ያስረዱት ኃላፊው፣ባለንብረቶች ያስመዘገቡትን የጦር መሣሪያ ላልተፈለገ ተግባር እንዳያውሉ አስጠንቅቀዋል።

ባለንብረቶቹ ፈቃድ ሲወስዱ የግል ንብረታቸውንም ሆነ የአካባቢያቸውን ፀጥታ እንዲጠብቁበት መሆኑን መረዳት ያሻል ያሉት አቶ መኳንንት፣ያለአግባብ ጥይት መተኮስ እንደሌለባቸው አስገንዝበዋል።

የጦር መሣሪያዎችን በማህበራዊ አገልግሎት ተቋማት፣በሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች፣ ሰላማዊ ሰልፍ በሚካሄድባቸው ስፍራዎች፣ በሃይማኖት ተቋማት፣ በመጠጥ ቤቶችና ሆቴሎች እንዲሁም በገበያ ቦታ ይዞ መንቀሳቀስ ክልክል መሆኑንም አስታውቀዋል።

ያለአግባብ ጥይት የሚተኩሱ ሰዎችን በመምከርና ወደ ሕጋዊ መንገድ ማምጣት የሁሉንም አካል ጥረት ይጠይቃል ያሉት አቶ መኳንንት፤ ተመክረው በማይመለሱ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቅቀዋል።

ከዚህ ቀደም 2001 ወዲህ ከሕግ ውጭ በሆነ መንገድ መሣሪያቸውን የተነጠቁ ግለሰቦችም ጉዳዩ ተጣርቶ መሣሪያቸው እንደሚመለስላቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም