የስንዴ ሰብላችን በዋግ በሽታ በመጠቃቱ ለጉዳት ተዳርግናል – የቤንች ማጂ ዞን አርሶ አደሮች

1239

ሚዛን ታህሳስ 19/2011 የስንዴ ሰብላቸው በዋግ በሽታ በመጠቃቱ ለጉዳት መዳረጋቸውን አስተያየታቸውን የሰጡ የቤንች ማጂ ዞን ስንዴ አምራች አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡

አርሶ አደሮቹ እንደሚሉት በዋግ በሽታ የተጠቃው ለመጀመሪያ ጊዜ የዘሩት ህዳሴ የተሰኘው የስንዴ ዘርያ ነው፡፡

አርሶ አደር ዘማች ዘውዴ ሸዋ በቤንች ወረዳ የኩላ ጋቻ ቀበሌ ነዋሪ  ሲሆኑ ሁለት ሄክታር ላይ የተዘራ የስንዴ ማሳቸው በዋግ መመታቱን ይናገራሉ፡፡

በዘንድሮ ዓመት የዘሩት ስንዴ ዘር በግብርና ጽህፈት ቤት በኩል የመጣና ከዚህ ቀደም ዘርተውት እንደማያውቁ ገልፀዋል፡፡

የስንዴ ዝርያው አበቃቀሉና ዕድገቱ ከሌሎች ዝርያዎች የተሻለ እንደነበር የገለፁት አርሶ አደሩ በፍሬ መያዣው ወቅት ላይ ግን ለብልሽት እንደተዳረገ ገልጸዋል፡፡

የዋግ በሽታው ስንዴውን ሙሉ በሙሉ ፍሬ አልባ ስላደረገውም ለኪሳራ መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

”አካባቢው በስንዴ አምራችነትና በምርታማነቱ የሚታወቅ ተስማሚ የአየር ንብረት ያለው ቢሆንም ዘንድሮ የዘራነው አዲስ የስንዴ ዘር ግን ያለምርት እንድንቀር አድርጎናል” ብለዋል፡፡

የተከሰተውን የስንዴ ዋግ በሽታ ለማጥፋት ጸረ ተባይ መድኃኒት በመርጨት ጥረት ቢደረግም ሊጠፋ አለማቻሉን የገለጹት ደግሞ ሌላኛው አርሶ አደር ጋኪኔ መልካ ናቸው፡፡

ከእርሻ ወቅት ጀምሮ አስፈላጊውን እንክብካቤ እንዳደረጉና ሰብሉም በጥሩ ሁኔታ ማደጉንም ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በየዓመቱ ስንዴ በመዝራት እንደሚተዳደሩ ገልጸው ”የተሻለ ዘር ነው በሚል የተሰጠን የስንዴ ዘር ለኪሳራ ዳርጎናል” ብለዋል፡፡

አቶ ቆጭቶ ባዩ የኩካ ቀበሌ ነዋሪ ግማሽ ሄክታር ስንዴ መዝራታቸውን ገልጸው በተከሰተው ቢጫ ዋግ በሽታ ከጥቅም ውጭ እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡

የስንዴው ዘር ቡቃያ ጀምሮ ለፍሬ እንስኪደርስ ድረስ የተሻለ ሰብል እንደሚመስል የሚናገሩት አርሶአደሩ ”የስንዴው ዛላ ሲታሽ ግን ባዶ ነው” ይላሉ፡፡

ከዚህ ቀደምም በተመሳሳይ የቢጫ ዋግ ተከስቶ እንደሚያውቅና በጸረ ተባይ መድኃኒት መቆጣጠር ይቻል እንደነበር አስታውሰው ”የዘንድሮው ለበሽታው በቀላሉ ተጋላጭና ለመቆጣጠርም አስቸጋሪ ነው” ብለዋል፡፡

የቤንች ማጂ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘማች በዛብህ በበኩላቸው በዘንድሮው የመኸር ወቅት 2ሺህ 230 ሄክታር መሬት በስንዴ ዘር መሸፈኑን ገልፀዋል፡፡

ከዚሁ ማሳ ውስጥ 510 ሄክታሩ  በዋግ በሽታ መጠቃቱን ተናግረዋል፡፡

አርሶደሮቹ የዘሩት ህዳሴ የተባለው አዲሱ የስንዴ ዘርያ ምንም እንኳን በሽታ የመቋቋም አቅሙ አነስተኛ ቢሆንም ችግሩ ከስንዴ ዝርያው ብቻ አለመሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ዘማች እንዳሉት በአካባቢው ተከስቶ  የነበረው ፖለቲካ  ሁኔታ ጸረ ተባይ መድኃኒት ርጭት በወቅቱ እንዳይከናወን እንቅፋት ሆኗል።

”በወቅቱ መርጨት አለመቻሉም የስንዴ ዋጉ እንዲባባስና በሰብሉ ላይ ጉዳት  እንዲያደርስ አድርጓል” ብለዋል።

የከፋ ጉዳት የደረሰባቸው አርሶደሮች ተለይተው የዘርም ሆነ ሌላ ድጋፍ እንዲደረግላቸው  ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚመከር አቶ ዘማች ጨምረው ገልፀዋል፡፡