ሸካ ዞን ወደ ሰላማዊ ሁኔታ እየተመለሰ መሆኑ ተጠቆመ

61

ሚዛን ታህሳስ 18/2011 በደቡብ ክልል ሸካ ዞን ተፈጥሮ የነበረውን የሰላም መደፍረስ ወደ ቀድሞ ይዞታው እንዲመለስ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ እየተሰራ መሆኑን  የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

በዞኑ በተለይም የኪ ወረዳና ቴፒ ከተማ በሰላም ዕጦት ለአራት ወር ተኩል ተቋርጠው የነበሩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች እየጀመሩ መሆናቸው ተገልጿል ።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ የሺዋስ ዓለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት በአካባቢው ተከስቶ በነበረ ግጭት በግልና በመንግስት የሚሰጡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ተቋርጠው ቆይተዋል ።

በዚህም "አገልግሎቶች ተቋርጠው በመቆየታቸው ህብረተሰቡ ለጉዳት ተዷርጓል" ብለዋል ።

ችግሩን ለመፍታት አስተዳደሩ በየደረጃው ከሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በጀመረው ውይይት አንጻራዊ ሰላም እየሰፈነ በመሆኑ የመንግስትና የግል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎት እየጀመሩ መሆኑን ተናግረዋል ።

"ትምህርት ቤቶች ተከፍተዋል፤ የመንግስት መስሪያ ቤቶችም ስራ እየጀመሩ ነው" ያሉት ዋና አስተዳዳሪው የተፈናቀሉ ዜጎችን የመመለስና የማቋቋም እንዲሁም የተዘረፉ ንብረቶችን የማስመለስ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል ።

እስካሁን የተቋረጠውን ትምህርት ማካካስ የሚያስችል ስራ እንደሚሰራ ተናግረው "በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ቴፒ ካምፓስ ተማሪዎችን መቀበል እንዲችል ውይይት እየተካሄደ ነው" ብለዋል፡፡ 

በአካባቢው ለወራት በዘለቀው የሠላም መደፍረስ ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው ከ32 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ እርቀው መቆታቸውን ዋና አስተዳዳሪው  አስታውሰዋል ።

በግጭቱ ከ6ሺህ 200 በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውንና 250 ቤቶች ተቃጥለው የግለሰቦች ንብረት መዘረፋቸውንም ጠቅሰዋል።

"ከግጭቱ ጋር በተያያዘ 16 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸው በህግ እየታየ ነው" ሲሉ ገልፀዋል፡፡

የዞኑ ሠላማዊ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ወደነበረበት እንዲመለስ የተጀመረው ህብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዋና አስተዳዳሪው አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም