ፍርድ ቤቱ በሰብዓዊ መብት ጥሰት በተጠረጠሩት መአሾ ኪዳኔና ሐዱሽ ካሳ ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ

70

አዲስ አበባ ታህሳስ18/2011 የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሰብዓዊ መብት ጥሰት በተጠረጠሩት መአሾ ኪዳኔና ሐዱሽ ካሳ ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ።

የሁለቱን ተጠርጣሪዎች ጉዳይ የያዘው መርማሪ ፖሊስ አንድ ተጨማሪ ሚስጥራዊ የማሰቃያ እስር ቤት ማግኘቱን አስታውቋል።

ፖሊስ ዛሬ ለፍርድ ቤቱ እንዳስታወቀው በሁለቱ ተጠርጣሪዎች ላይ ቀሪ የምርመራ ስራዎች ስላሉኝ በሚል የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቆ ነበር።

የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደሕንነት  አገልግሎት መስሪያ ቤት ሰራተኞች የነበሩት መአሾ ኪዳኔና ሐዱሽ ካሳ ዛሬ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል።

ከሁለቱ ተጠርጣሪዎቹ መካከል አቶ መአሾ ኪዳኔ በብሔራዊ መረጃና ደሕንነት አገልግሎት ዋና መስሪያ ቤት ለረጅም ዓመት የዋና ዳይሬክተር ልዩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሆነው በሚሰሩበት ወቅት በሕግ የተሰጣቸውን ስልጣን ያለአግባብ ተጠቅመዋል በሚል ነው ፍርድ ቤት የቀረቡት።

በተለይም በዋና ወንጀል አድራጊነት ከተጠረጠሩት ከኃላፊው አቶ ጌታቸው አሰፋ ጋር በመመሳጠር በቀጥታ በሚሰጣቸው ሕገ-ወጥ ትዕዛዝና በራሳቸው ጊዜ ሕግን በመተላለፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አካሂደዋል በሚል ነው የተጠረጠሩት።

አቶ መአሾ በወቅቱ በሽብር ወንጀል የተፈረጁ ሰዎችን ኦነግ፣ ግንቦት ሰባት፣ ኦብነግና የሐይማኖት አክራሪ አባላት ናችሁ በሚል በሕግ የመያዝና የማሰር ስልጣን ሳይኖራቸው ተጠርጥራችኋል በማለት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያደርሱ ነበር በሚልም መጠርጠራቸውን አመልክቷል።

አቶ ሐዱሽ ካሳም እንዲሁ በድብቅ እስር ቤቶች ውስጥ ያለአግባብ ታስረው በሚገኙ ግለሰቦች ወንጀል እንዲፈፀምባቸው በማድረግና በማስደረግ መጠርጠራቸው ነው የተገለፀው።

በተጨማሪም ሁለቱ ተከሳሾች ምንጩ ያልታወቀ ሃብት በማካበትም በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።

ፖሊስ በአሁኑ ወቅት ተጨማሪ የተጎጂዎችና የምስክሮች ቃል መቀበል የሕክምና ማስረጃ ማሰባሰብ፣ የምርመራ ቡድን ማቋቋምና ሌሎች ቀሪ ስራዎች ስላሉኝ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ይፈቀድልኝ በማለት ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱም ከታሕሳስ 15 ቀን ጀምሮ የሚታሰብ 10 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በመፍቀድ ለታሕሳስ 25 ቀን 2011 ዓም ቀጠሮ ይዟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም