ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የአምስት አገራት አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ ተቀበሉ

1420

አዲስ አበባ ታህሳስ 18/2011 የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የአምስት አገራት አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ ተቀበሉ።

ፕሬዝዳንቷ የተቀበሉት የሶማሊያ፣ ግብጽ፣ ኤርትራ፣ቱኒዝያና ታይላንድ አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ   ነው።

ከተሿሚዎቹ መካከል ኢዜአ ያነጋገርናቸው አምባሳደሮች ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገልፀውልናል።

ከ20 አመታት በኋላ ኤምባሲዋን በኢትዮጵያ የከፈተችው የኤርትራ አምባሳደር ሰመረ ርዕሶም የሁለቱ አገራት የመራራቅ ምእራፍ አብቅቶ አገራቸውን ወክለው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣታቸው መደሰታቸውን ገልፀዋል።

የሁለቱ አገሮች ጠንካራ ወዳጅነት ከራሳቸው ባለፈ ለአፍሪካም በብዙ መልኩ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑንም አምባሳደሩ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታም የኢትዮ-ኤርትራን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ የኢኮኖሚ ትስስር እንዲሁም ሌሎች ትብብሮችን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ የሶማሊያ አምባሳደር አሊ ሼሪፍ በበኩላቸው በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የሰላምና የጸጥታ እንዲሁም ሌሎች ግንኙነቶችን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

በግብጽና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት ወደ እስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማሳደግ እንደሚሰሩ የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ የግብጹ አምባሳደር ኦሳማ አብደልካሃሊክ ናቸው።

የቱኒዝያና ታይላንድ አምባሳደሮችም አገሮቻቸው ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ዘርፎች የሚኖራቸውን ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው ከአገራቱ ጋር ቀደም ሲል የተፈረሙ ስምምነቶችን ስራ ላይ ለማዋል እንዲሰሩ ለአምባሳደሮች መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም ተናግረዋል።

ከጎረቤት አገሮች ጋር በጋራ ለመስራት የኢትዮጵያ መንግስት ትኩረት መስጠቱንም ፕሬዝዳንቷ አስረድተዋል።