በኦሮሚያ ክልል ግጭት የሚፈጥሩ ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል-ኦብኮ

116

አዲስ አበባ ታህሳስ 18/2011 የኦሮሚያ ክልልን የጦር ቀጠና ለማድረግ የሚጥሩ ኃይሎች እጃቸውን ሊያነሱ ይገባል አለ የኦሮሞ ብሄራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ)።

ፓርቲው በኦዴፓና ኦነግ መካከል የተፈጠረው ግጭት የንፁሃንን ዜጎች የመኖር ዋስትናና ሰላም ላይ ችግር እያስከተለ በመሆኑ በፍጥነት ሊቆም ይገባል ብሏል።

የኦብኮ ሊቀ-መንበር አቶ ቶሎሳ ተስፋዬ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት "ባለፉት ዓመታት በኦሮሞም ሆነ በሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ ይደርስ የነበረው ግፍ ተለውጦ የዴሞክራሲ ምህዳሩ እየሰፋ ቢሆንም ለውጡን ለማደናቀፍና በዜጎች መካከል ግጭት ለመፍጠር ስራ ያልፈቱ አካላት ተግባራቸውን ገፍተውበታል"።

"አገሪቱን ለማመስ ፍላጎት ያላቸው አካላት ከኢትዮጵያዊያን በተዘረፈ ገንዘብ በሚገዛ መሳሪያ በተለይም በኦሮሚያ ላይ ግጭት እየፈጠሩ ነው" ሲሉ ተናግረዋል። በሞያሌ፣ በጉጂና በሻሸመኔ አካባቢ እየታዩ ያሉ ግጭቶችን አንስተዋል።

ለዘመናት የነበረን አብሮነት በመናድ በዜጎች መካከል ክፍፍል እንዲፈጠር በማድረግ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀል ምክንያት ሆነዋልም ብለዋል።

"በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ብቻ ስልጣን ለመያዝ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር መስማማት ላይ የተደረሰበት ጊዜ በመሆኑ በመሳሪያ ሊያዝ የሚችል ስልጣን አለመኖሩን በፓርቲዎችም ይሁን በህዝቡ ዘንድ አመኔታ አግኝቷል" ነው ያሉት።

ሆኖም በኦነግና በኦዴፓ መካከል እየተፈጠረ ባለ በመሳሪያ የታገዘ ግጭት በምዕራብ ወለጋ ሆሮ ጉዱሩ፣ በደምቢዶሎ፣ በቄለም ወለጋ እንዲሁም በሰሜን ኦሮሚያ በኩዩ አካባቢ ላለፉት ሶስት ቀናት መረጋጋት ጠፍቷል።

"ኦነግ ወደ አገር ቤት ሲገባ የተደረገው ስምምነት በግልፅ ለህዝብ ባለመቅረቡ አሁን ለተፈጠረው ጦርነት ማወጅ ምክንያት ሆኗል" ብለዋል ሊቀ-መንበሩ።

በመንግስትም በኩል ኃይል መጠቀም የዜጎችን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ በውይይት ለመፍታት ጥረት መደረግ እንዳለበት ተናግረዋል።

የፓርቲው የድርጅት ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ታከለ አዱኛ በበኩላቸው ወደ ስልጣን መምጣት የሚቻለው በምርጫ ብቻ ነው ካሉ በኋላ "በኦነግ በኩል የሚደረግ የመንግስትን መዋቅር የማፍረስና መንገድ የመዝጋት ተግባር ሊቆም ይገባል" ብለዋል።

መንገዶች በመዘጋታቸው ኢኮኖሚው መጎዳት፤ ዜጎችም እንዳይንቀሳቀሱ መደረግ የለበትም ነው ያሉት።

ፓርቲው እነዚህ ጉዳዮች ከግንዛቤ በማስገባት ባለሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ ማውጣቱን አስታውቀዋል።

ግጭቶች ቆመው ህዝቡ በመስዋዕትነት ያገኘውን ነፃነት እንዲቀጥልና ለውጡን የማይፈልጉ ኃይሎች መጠቀሚያ እንዳይሆን ጥሪ አቅርበዋል።

"የስልጣን ጥመኞችና ሌቦችም በዚህ መልኩ የሚያዝ ስልጣን ባለመኖሩ ከዴሞክራሲ ኃይሎች ጋር በመደመር ወደ ትክክለኛ መስመር ሊመለሱ ይገባል" የሚለው የመግለጫው አቋም ነው በማለት አብራርተዋል።

ፍትሃዊ ምርጫ የሚረጋገጠው አገር ሰላም ስትሆን በመሆኑ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎችና ድርጅቶች ለውጡን ለማስቀጠል መስራት አለባቸውም ይላል የአቋም መግለጫው።

በኦሮሚያ ክልል እየተፈጠረ ያለውን ግጭት ለማስቆምና ሰላምን ለማረጋገጥ በኦሮሞ ስም የተደራጁ ፓርቲዎችም በጋራ መስራት እንዳለባቸውና ኦብኮ ለውጡን ለማስቀጠልና የህዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ ከመንግስት ጎን እንደሚቆም ጭምር አረጋግጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም