በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል የመልካምድር እንጂ ልባዊ ድንበር የለም…ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ

3767

ካርቱም ሚያዚያ25/2010 በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል የመልካምድር እንጂ ልባዊ ድንበር አለመኖሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ አህመድ ትላንት ማምሻውን ከሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሃሰን አልበሽር ጋር በሱዳን ብሔራዊ ቤተ-መንግሥት ተወያይተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከሱዳን ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሀመድ አብደላ ጋር ትላንት ምሽት ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል የመልካምድር እንጂ ልባዊ ድንበር አለመኖሩን ዶክተር ወርቅነህ ጠቁመዋል።

ሁለቱ ህዝቦች አንድ ህዝብ፤ የአባይ ልጆች መሆናቸውንና በአገራት መካከል ድንበር ቢኖርም መሬት ላይ እንጂ ልባቸው ውስጥ አለመኖሩን ገልጸዋል።

ጉብኝቱም በአገራቱ መካከል ለበርካታ ጊዜያት የቆየውን ታሪካዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል ብለዋል።

የሱዳን ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በሱዳን ጉብኝት ማድረጋቸው አስደስቶናል ብለዋል።

የኢትዮጵያና ጎረቤት አገር ሱዳን ግንኙነት የተጀመረው በአራተኛው ክፍለ ዘመን በአክሱምና በሱዳኑ የሜሮይ ሥልጣኔ በነበረበት ወቅት ነበር።

ከዛም ጊዜ አንስቶ የሁለቱ አገራት ግንኙነት በተለይም በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ ጠንካራና ለአሁኑ አጋርነት መሰረት መጣሉን መረጃዎች ያሳያሉ።

አገራቱ ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከጀመሩ በኋላም ያሏቸውን ማኅበራዊ ግንኙነቶች በኢኮኖሚና በፖለቲካ መስክ አጠናክረውታል።

በተለይም በአገራት መሪዎችና በከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ደረጃ የተደረጉት ይፋዊ የሥራ ጉብኝቶችም ለዚሁ ግንኙነት መዳበር አበርክቷቸው የላቀ ነበር።

በምጣኔ ኃብት መስኮች ላይ ያሏቸውን የትብብር አድማሶች ለማስፋት የጋራ የኢኮኖሚ ኮሚሽንም አቋቁመው እየሰሩ ሲሆን እአአ ከ2013 ጀምሮ የተለያዩ የስምምነት ማዕቀፎችን በማጽደቅም ጭምር  አጽንተውታል።

የንግዱ ዘርፍ ግንኙነትም፤ ኢትዮጵያ የግብርና ምርቶችን ወደ ሱዳን በመላክ በአንጻሩ ሱዳን የነዳጅ ጋዝን  ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ላይ ያመዘነ ነው።

ለአብነትም ባለፈው ዓመት የሁለቱ አገራት የንግድ ልውውጥ 300 ሚሊዮን ዶላር መድረሱን ነው መረጃዎች የሚያሳዩት።

ኢትዮጵያም በየዓመቱ 100 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለሱዳን በመሸጥ በየዓመቱ 80 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢም ታስገባለች።

በተጓዳኝ ከ800 በላይ የሱዳን ባለኃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ የተሰማሩ ሲሆን በኢትዮጵያ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ካፈሰሱ አገራት ተርታ ሱዳን አንዷ ናት።

ኢትዮጵያና ሱዳን ከአየር ትራንስፖርት በተጨማሪ በመንገድም የተገናኙ አገራት ሲሆኑ በቀጣይ ደግሞ ልክ እንደ ጅቡቲ በባቡር መስመር ለመተሳሰር እቅድ መኖሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።

በፖለቲካውም መስክ የጋራ አቋምን በመያዝ በአፍሪካ ቀንድና አከባቢው ላይ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ቀጠናዊ ትብብር አሏቸው።

ኢትዮጵያና ሱዳን ‘የታላቁ ህዳሴ ግድብ ለቀጠናው አገራት ምጣኔ ኃብታዊ ውህደት ያመጣል’ በማለትም የጋራ አቋም የሚያንጻባርቁ አገራትም ናቸው።

ያም ብቻ ሳይሆን ግድቡ ለቀጠናው አገራትም ጭምር የተናጠል ጥቅም እንደሚሰጥ በጽኑ ያምናሉ።

በአፍሪካ በሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ ላይ የምትገኘው ሱዳን፤ በቆዳ ስፋቷ ከአፍሪካ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ከ41 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይዛለች።

ጎረቤታሞቹ ኢትዮጵያና ሱዳን ከሰባት መቶ ኪሎ ሜትር በላይ የሚያዋስናቸውን የጋራ ድንበርን ይጋራሉ።