በኦነግ ስም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 23 ታጣቂዎች እጃቸውን ሰጡ

90

ፍቼ ታህሳስ 17/2011 በኦነግ ስም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 23 ታጣቂዎች   በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ተስማምተው በኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ ዞን ለወረጃርሶ ወረዳ ፖሊስ እጃቸውን ሰጡ፡፡

የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር መንግስቱ ከተማ እንደገለፁት ትናንትናና ዛሬ እጃቸውን ከነሙሉ ትጥቃቸው የሰጡት እነዚህ ሰዎች  ከስድስት ወር  እስከ ሁለት  ዓመት በጫካ ውስጥ በኦነግ  አመራር ሰጪነት  ሲታገሉ የቆዩ ናቸው፡፡

ታጣቂዎቹ በምዕራብና ሰሜን ሸዋ ዞን መካከል በሚገኘው ሙገር ወንዝና በረሃ በሚገኙ ሸለቆዎች እንዲሁም በወለጋ የተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ እንደነበር አመልክተዋል፡፡

በሀገር ሽማግሌና በመንግስት የተደረገውን ጥሪ ተቀብለው በሰላማዊ መንገድ ለመስራት ተስማምተው እጃቸውን መስጠታቸውን ኢንስፔክተሩ አመልክተው በተመሳሳይ ታጥቀው የተሰማሩ ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲገቡ  ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

እጃቸውን በሰላማዊ መንገድ ከሰጡት መካከል የ33 ዓመት እድሜ ያለው መንግስቱ ለገሰ በሰጠው አስተያየት ካለፈው ዓመት  ጀምሮ በኦነግ አመራር ሰጪነት  ሲንቀሳቀስ መቆየቱን ተናግሯል፡፡

በአሁኑ ወቅት  መንግስትና ህዝብ ያደረጉላቸውን  ሰላማዊ ጥሪ ተቀብለው መመለሳቸውን ጠቅሶ በወረጃርሶ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች የሀገር ሽማግሌዎችና ነዋሪዎች የሰጧቸው ምክርና መልካም አቀባበል መልሰው ህዝቡን ለመካስ እንዳነሳሳውም ገልጿል፡፡

ሌላው አስተያየት ሰጪ የቡድኑ  አባል ወጣት ከተማ አዱኛ እንዳለው  ወደ ቡድኑ ከተቀላቀለ ስድስት ወራት ሆኖታል፡፡

በተፈጠረው ምቹ የለውጥ ሁኔታም በሰላም ለመኖር በመወሰን እጁን እንደሰጠ ገልጾ መንግስት በሚያሰማራው የሰላምና የፀጥታ ስራ  አካባቢውን መጥቀም እንደሚፈልግም ተናግሯል፡፡

በተለይ ህዝቡ የመብቱና የሀገሩ ሀብት ተጠቃሚ እንዲሆን በሰላማዊ መንገድ ትግሉን እንደሚያካሂድም ጠቅሶ መንግስት የጀመረውን ሰላማዊ  የለውጥ ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩሉን እገዛ እንደሚያደርግ አስረድቷል፡፡

ወጣት ባሕሩ ገመቹ በበኩሉ ለሰባት ወራት  በጫካ ውስጥ እንደቆየ ተናግሮ የኦሮሞን ልጆች መብት ለማስከበር በተሳሳተ መንገድ የትጥቅ ትግሉን አማራጭ አድርጐ ተጉዞ እንደነበር ገልጿል፡፡

አካሄዱ እንደማያዋጣ ተገንዝቦ በሰላማዊ መንገድ ለመንግስት የፀጥታ ኃይል  እጅ ሰጥቶ ወደ ስራ ለመሰማራት እንደተዘጋጀ ተናግሯል፡፡

በአካባቢው የሀገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ  ቶልቻ  አለሙ ህዝብና መንግስትን የሚያቀራርብ  ተግባራትን በመስራት  ወደ ጫካ የገቡ ወገኖች እንዲመለሱ  የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚቀጥሉ  ገልጸዋል፡፡

ሰላምን የሚያደፈርሱ አካላትን በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ የአካባቢው ህዝብና መንግስትን አስተባብረው እየሰሩ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ 

በዞኑ ለፀጥታ ስጋት የሆኑ አካባቢዎችን በሃገር መከላከያ ሰራዊትና በክልሉ የፀጥታ ኃይል ትብብር  ለማስከበር  የተጠናከረ ስራ እያካሄዱ መሆናቸውን የዞኑ  ፀጥታና አስተዳደር መስሪያ ቤት ኃላፊ አቶ ለማ ወርዶፋ  አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም