መሰረተ ልማቶችን አቀናጅቶ ተግባራዊ አለማድረግ የዕቅዱ አፈጻጸም ዋነኛ ተግዳሮት ነው

42
አዲስ አበባ ግንቦት 17/2010 መሰረተ ልማቶችን አቀናጅቶ ተግባራዊ አለማድረግና የገበያ ትስስር እጥረት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመካከለኛ ዘመን አፈፃፀም ቀዳሚ ተግዳሮት እንደነበር የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ። የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ባለፉት አራት ቀናት በአገር አቀፍ ደረጃ የተካሄደውን የምክክር መድረክ መጠናቀቅ አስመልክቶ ከህብረተሰቡ የተገኙ ግብአቶችን ዛሬ ለጋዜጠኞች ይፋ አድርጓል። ምክትል ኮሚሽነር አቶ ጌታቸው አደም በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ለቀጣይ የዕቅድ ዘመን ግብዓት የሚሆኑ አስተያየቶች በመላው አገሪቱ በተደረጉ የምክክር መድረኮች ተነስተዋል። በዚህም የመንገድ፣ የመብራት የቴሌኮምና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን አቀናጅቶ አለመተግበር በሁሉም አካባቢዎች መንግስትን ዋጋ ከማስከፈል አልፈው የህብረተሰቡን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በማወክ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ቀንሷል። በግብርና ምርቶች በተለይም በአትክልትና ፍራፍሬ ከተለመደው የአስተራረስ ዘዴ በመውጣት የተገኙ ትሩፋቶች በገበያ ትስስር ማነስ የሚፈለገውን ውጤት አለመምጣታቸው ተገልጿል። በዚህና በሌሎችም ምክንያቶች በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመካከለኛ ዘመን አፈፃፀም በግብርናው ዘርፍ የተገኘው አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆኑን አቶ ጌታቸው ተናግረዋል። የትምህርት ጥራት መጓደል፣ የመልካም አስተዳደር፣ በእንስሳት ዘርፍ ያለውን እምቅ ሃብት ያለመጠቀም ችግር የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ በአግባቡ ለወጣቶች የስራ ዕድል ያለመጠቀም ችግር በቀጣይ ትኩረት ተሰጠቶ ሊሰራባቸው እንደሚገባ የህብረተሰብ ክፍሎቹ ጠቁመዋል። እንዲህ ዓይነት የምክክር መድረኮች ሲካሄዱ በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ጌታቸው መንግስት ለዚህ ማስፈጸሚያ 10 ሚሊዮን ብር በጀት መድቦ መንቀሳቀሱን ጠቅሰዋል። በዚህም ከህብረተሰቡ ለቀጣይ ዕቅድ ዝግጅት ግብዓት የሚሆኑ አስተያየቶች እንደተገኙና የተካሄደው የምክከር መድረክ ዓላማውን ያሳካ መሆኑን ጠቁመዋል። ውይይቱ የሴቶችና ወጣቶች፣ የአርሶና አርብቶ አደሮች፣ የግሉ ዘርፍና የሲቪል ማሕበረሰብ ተብለው በተከፋፈሉ በ12 የክልል ማዕከላት 48 የምክክር መድረኮች መካሄዱ ተገልጿል። የ2008ና የ2009 በጀት ዓመት ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ዕድገቱ በአማካኝ 9 ነጥበ 45 በመቶ እድገት አስመዝግቧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም