የህዳሴ የሰላም ዋንጫ በምዕራብ ዕዝ የ12ኛ መተማ ክፍለ ጦር አባላት አቀባበል ተደረገለት

105
ነቀምቴ ግንቦት 17/2010  የህዳሴ የሰላም ዋንጫ በምዕራብ ዕዝ የ12ኛ መተማ ክፍለ ጦር  ሲደርስ ደማቅ አቀባበል ተደረገለት፡፡ የክፍለ ጦሩ አባላት ለዋንጫው አቀባበል ያደረጉለት ትናንት በደዴሳ ወታደራዊ ማስልጠኛ ማዕከል ነው፡፡ የምዕራብ ዕዝ ስታፍ ኢንዶክትሪኔሽን ዳይሬክተር ብርጋዲዬር ጀነራል ተስፋዬ ተመስጌን ዋንጫውን ለ12ኛ መተማ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ብርጋዲዬር  ጀነራል ብርሃኑ ጥላሁን አስረክበዋል። በርክክቡ ወቅት ብርጋዴር ጀነራል ተስፋዬ  ተመስጌን እንደገለጹት  ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መላው የሀገሪቱን ሕዝቦች ያስተሳሰረና ለልማት በአንድነት ያሰለፈ ነው። ለግድቡ ግንባታ እውን መሆን ህዝቡ ከዳር እስከ ዳር የነቃ ተሳትፎ እንዳሳየው ሁሉ የሰራዊቱ አባላትም የሀገሪቱን ዳር ድንበር ከማስከበር በተጓዳኝ የቦንድ ግዥ በማከናወን ላቅ ያለ ተግባር እየፈጸሙ መሆናቸውን ተናግረዋል። "የዚህ ግዙፍ ፕሮጀክት ግንባታ በቀጠናችን ውስጥ የሚካሄድ በመሆኑ ሰራዊቱ ከሚያደርገው ጥበቃና ከለላ ባሻገር እስካሁን በስድሰት ዙር የቦንድ ግዥ አከናውኗል" ብለዋል። ዋንጫው በዕዙ ጠቅላይ መምሪያ በነበረው ቆይታ ከስድስት ሚሊዮን 600ሺህ ብር በላይ  የቦንድ ግዥ መፈጸሙንም ጠቅሰዋል። የ12ኛ መተማ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል  ብርሃኑ ጥላሁን በበኩላቸው  የህዳሴው የሰላም ዋንጫ ይዞት የመጣውን ዓላማ ለማሳካት የሰራዊቱ አባላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። ከክፍለ ጦሩ አባላት መካከል ወታደር ጽጌሬዳ ዳዊት በሰጡት አስተያየት የህዳሴው የሰላም ዋንጫ ወደ አካባቢያቸው መምጣቱ እንዳስደሰታቸው ገልጸው እስካሁን የ5 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የዋንጫውን መምጣት ተከትሎ ተጨማሪ ቦንድ በመግዛት እንደሚሳተፉም አመልክተዋል። ቀደም ሲል ለህዳሴው ግድብ ድጋፍ ማድረጋቸውንና  ለወደፊቱም ተሳትፏቸውን እንደሚያጠናክሩ የገለጹት ደግሞ ሌላው የክፍለ ጦሩ አባል ሃምሳ አለቃ በቀለ በድሉ ናቸው። ዋንጫው በምዕራብ ዕዝ 24ኛው ፣5ኛው፣  42ኛው ክፍለ ጦሮች እና በዕዝ ጠቅላይ መምሪያ የነበረውን ቆይታ አጠናቆ ነው ትናንት 12ኛው መተማ ክፍለ ጦር የደረሰው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም