ፍርድ ቤቱ በሌተናል ኮሎኔል ሰጠኝ ካህሳይ ላይ ፖሊስ የጠየቀውን የምርመራ ጊዜ ፈቀደ

71

አዲስ አበባ ታህሳስ 17/2011 የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሌተናል ኮሎኔል ሰጠኝ ካህሳይ ላይ ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ።

ሌተናል ኮሎኔል ሰጠኝ ካህሳይ ፍርድ ቤት የቀረቡት መረጃን በማጥፋትና በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ነው።

በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪው ላይ ለሚደረግ ተጨማሪ ምርመራ ፖሊስ የጠየቀውን 10 ቀናት በመፍቀድ ለታህሳስ 25 ቀን 2011 ዓም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ተጠርጣሪው  የብረታ ብረት ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ኩባንያ በሆነው ሃይቴክ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ የሰው ሃብት አስተዳደር ሆነው በሚያገለግሉበት ወቅት ስራ አስኪያጁ ለስራ ጉዳይ በሌሉበት ወቅት ውክልና ተሰጥቷቸው ሳለ በአፋጣኝ የኩባንያውን ማኔጅመንት በማሳመን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ትራንስፎርመር እንዲያቀርብ የግዢ ውል በመፈረምና ወልዳይ ገብረማርያም ብቸኛ አስመጪ በሚል ያለምንም ጨረታ ግዥ በመፈጸም በመንግስትና ህዝብ ሃብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል በሚል ፖሊስ በሙስና ወንጀል የጠረጠራቸው  መሆኑን  ቀደም ሲል መዘገባችን ይታወሳል ።

እንዲሁም ተጠርጣሪው ህጉን ያልተከተለ የ15 ሚሊዮን ብር ግዢ እንዲፈጸም በማድረግ በአገርና በህዝብ ንብረት ላይ ጉዳት እንዳደረሱም ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ማስረዳቱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም