የመጠጥ ውሃ ችግር እንዳጋጠማቸው የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተናገሩ

56

ሶዶ ታህሳስ17/2011 የመጠጥ ውሃ ችግር በትምህርታቸው ላይ ተጽዕኖ እያሳደረባቸው መሆኑን በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የዋናው ግቢ ተማሪዎች ተናገሩ፡፡

ዩኒቨርስቲው በበኩሉ ችግሩ በውሀ መስመር ብልሽት የተከሰተ በመሆኑ ለማስተካከል ጥረት እያደረኩ ነው ብሏል፡፡

በተቋሙ የታሪክና ቅርስ ጥበቃ ትምህርት የሶስተኛ ዓመት ተማሪ ጽዮን ደመቀ እንዳለችው በግቢው ያለው የመጠጥ ውሃ ችግር የቆየ ቢሆንም ካለፈው ሳምንት አንስቶ ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ አገልግሎቱ የለም፡፡

ይህም በተለይ ለሴቶች ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን ጠቅሳ የመጸዳጃ ቤቶችን ለማጽዳት ባለመቻሉ የተፈጠረው መጥፎ ሽታው ለጤና ጠንቅ እንደሆነባቸው ገልጻለች፡፡

ውሀ ምናልባት ከመጣ በሚል ለመቅዳት በማደሪያ ክፍል ያሉ ተማሪዎች በፈረቃ ከትምህርት እየቀሩ ለመጠበቅ መገደዳቸውንና በትምህርታቸው ላይም ጫና እያሳደረ እንደሚገኝ ጠቅሳለች፡፡

የስነልቦና ትምህርት የሶስተኛ ዓመት ተማሪ  ሲፈልግ ታምራት በበኩሏ" አቅም ያለው የታሸገ ውሃ ገዝቶ መጠቀም ችሏል፤ መግዛት የማንችለው ግን በጣም ተቸግረናል " ብላለች፡፡

ሌሊት ላይ ይመጣል በሚል በማይሆን ሰዓት ውሀ ፍለጋ ለመውጣት መገደዳቸውንና ይህም ለጾታዊ ትንኮሳ እንደዳረጋቸው ጠቁማለች፡፡

የውሃ ችግሩን ሰበብ በማድረግ ተማሪውን ለማወክና የመማር ማስተማር ስራውን ለማደናቀፍ ለሚጥሩ ግለሰቦች መንገድ እየከፈተ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስባለች፡፡

ከውሃ አቅርቦት እጥረት ጋር በተያያዘ ከዩኒቨርሲቲው አመራር ጋር በተደጋጋሚ ቢነጋገሩም መፍትሄ እንዳልተሰጠ የተናገረው ደግሞ የተማሪዎች ህብረት አባልና የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት አራተኛ ዓመት ተማሪ ፍሬው ሞገስ ነው፡፡

በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ኤፍሬም ጉልፎ  ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ በውሀ መስመር ላይ በተፈጠረ ብልሽት ምክንያት ችግሩ መከሰቱን አምነዋል፡፡

ችግሩንም ለመፍታት  የአጭርና የረጅም ጊዜ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዉ ለጊዜው ከሶዶ ከተማ ውሃ በማስመጣትና የታሸገ ውሃ በማደል እጥረቱን ለማቃለል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የተበላሸውን ለመጠገን እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ይህም በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ በቂ አገልግሎት የሚሰጥበት ሁኔታ እንደሚመቻች አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም