ፍርድ ቤቱ በኮሎኔል ደሴ ዘለቀ ላይ የክስ መመስረቻ ግዜ 14 ቀናትን ፈቀደ

73
አዲስ አበባ ታህሳስ 16/2011 የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በኮሎኔል ደሴ ዘለቀ ላይ የክስ መመስረቻ ግዜ 14 ቀናትን ፈቀደ። ኮሎኔል ደሴ ዘለቀ ዛሬ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ የወንጀል ችሎት ቀርበዋል። ፖሊስ በከፍተኛ የሙስና ወንጀል በጠረጠራቸውና የአዳማ እርሻ መሳሪያዎች ኃላፊ በነበሩት ኮሎኔል ደሴ ዘለቀ  ላይ ሲያካሒድ የቆየውን  ምርመራ በመጨረሱ ለአቃቤ ህግ መዝገቡን አስረክቧል። ኮሎኔል ደሴ ዘለቀ በሱማሌ ክልል ሀረዋና ኩለን፣ በአፋር ክልል ደግሞ ሱሉታ መስኖ ግንባታ ፕሮጀክቶች በሚሰሩበት ወቅት የሙስና ወንጀል ድርጊቶችን በመፈፀም በፕሮጀክቶቹ አፈፃፀም ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ በማድረግ ተጠርጥረዋል። በተጨማሪም በሕገወጥ መንገድ የትራክተሮች  ግዥ እንዲፈፀም በማድረግ በአገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ወንጀልም እንደተጠረጠሩ ነው ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ያስረዳው። በዚህ መሰረትም አቃቤ ሕግ መዝገቡን በመረከቡ ለፍርድ ቤቱ ካቀረበው የ15ቀን የክስ መመስረቻ ጊዜ ውስጥ ፍርድ ቤቱ 14 ቀናትን ፈቅዷል። በተመሳሳይም ፍርድ ቤቱ ከሰዓት በፊት በዋለው ችሎት በአለም ገነት የቆርቆሮ ፋብሪካ ባለቤት በአቶ አለም ፍጹም ላይም ፖሊስ ሲያካሒድ የነበረውን መረጃ የማሰባሰብ ስራ ማጠናቀቁን አስታውቋል። በዚህ መሰረትም ፍርድ ቤቱ በአቶ አለም ፍጹም ላይ የ10ቀናት የክስ መመስረቻ ጊዜን ፈቅዷል።                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም