በአካባቢ ጸጥታ ማስከበር ለተሰማሩ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ድጋፍ ተደረገ

59
ማይጨው ታህሳስ 16/2011  ግማሽ ሚሊዮን ብር በጸጥታ ማስከበር ስራ ለተሰማሩ የመኾኒ ከተማ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ድጋፍ ማድረጉን  በትግራይ ደቡባዊ ዞን የራያ አዘቦ ወረዳ አስተዳዳር ገለፀ። የገንዘብ ድጋፉን  ወጣቶቹ የጀመሩትን በጎ ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማበረታታ ያለመ  ነው፡፡ የወረዳው አስተዳዳር የህዝብ አደረጃጀት ኃላፊ አቶ ግርማይ ከላሊ የገንዝብ ድጋፍ በተለይ ወጣቶቹ እንቅስቃሴያቸው ላይ ለሚያጋጥማቸው የእለተ እለት የስራ ማስኬጃ የሚያውሉት መሆኑን አስረድተዋል። በመኾኒ ከተማ ከትናንት በስቲያ  በተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም  የተገኘው ይሄው ገንዘብ ከወረዳው የመንግስት ሰራተኞችና ከንግዱ ማህበረሰብ አባላት እንደሆነ ጠቅሰዋል። ከተሰበሰበው የድጋፍ ገንዘብ ውስጥ 326 ሺህ ጥሬ ገንዘብ በመኾኒ ከተማ ከሚኖሩ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ሲሆን ቀሪው የመንግስት ሰራተኞች ከወርሃዊ ደሞዛቸው ካዋጡት የተገኘ ነው ተብሏል፡፡ በገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሙ ከተሳተፉት መካከል የሜይዳ ራያ ሆቴል ባለቤት ዲያቆን ሞገስ ንጉሰ በሰጡት አስተያየት፣ " ያለወጣቶች ተሳትፎ የአካባቢ ዘላቂ ሰላም መጠበቅ አይቻልም"ብለዋል። ወጣቶቹ የከተማዋን ሰላም በማረጋገጥ ባከናወኑት ተግባር በመደሰታቸው የ10 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን አመልክተዋል። በተጨማሪም ለአንድ ዓመት የሚቆይና በየወሩ የአንድ ሺህ ብር ድጋፍ ለመስጠትም ወስነዋል፡፡ ወጣቶቹ  በፀጥታ ማስከበር ስራ በመሰማራታቸው ህዝብ በሰላም ወጥቶ  እንዲገባ በማስቻሉ የአምስት ሺህ ብር ድጋፍ መስጠታቸውን የተናገሩት ደግሞ በመኾኒ ከተማ  የትንሳኤ ሆቴል ባለቤት ወይዘሮ ብርሃን ኪዳነ ናቸው። የወጣቶቹ እንቅስቃሴ ይበልጥ እንዲጠናክረ ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታትም በየወሩ  የአንድ ሺህ ብር ድጋፍ እንደሚሰጡ አስታውቀዋል። በፕሮግራሙ ማብቂያ የዞኑ  ዋና አስተዳዳሪ አቶ ረዳኢ ሓለፎም እንደተናገሩት፣  ወጣቶቹ በራሳቸው ተነሳሽነት የጀመሩት የፀጥታ ማስከበር ስራ ለሌሎች ምሳሌ ነው። ሆኖም  ወጣቶቹ የህዝቡን ሰላም ሲጠብቁ ኑሯቸውን መጎዳት እንደማይኖርባቸው ጠቅሰው  "ለወጣቶቹ ዘላቂ የገቢ ምንጭ የሚሆን  የስራ ዕድል ለመፍጠር ትኩረት ይሰጣል"ብለዋል። ወጣቶቹ በፀጥታ ማስከበር ስራ በመንቀሳቀስ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች ይዘው በሚንቀሳቀሱና በህብረተሰቡ ሰላም ላይ ስጋት በሚፈጥሩ ግለሰቦች ላይ  ባደረጉት ቁጥጥር ውጤት ማምጣታቸውም ተመልክቷል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም