የኢትዮጵያ የምርት ገበያ የአኩሪ አተርና ሽምብራ ምርት ግብይት ሊጀምር ነው

81
አዲስ አበባ ታህሳስ 16/2011የኢትዮጵያ የምርት ገበያ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ የአኩሪ አተርና ሽምብራ ግብይት ወደ ዘመናዊ ስርዓቱ በማስገባት ምርቶቹን መቀበል እንደሚጀምር አስታወቀ። ምርት ገበያው ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ከታህሳስ 22 ቀን ጀምሮ በተዘጋጁት ቅርንጫፎች የአኩሪ አተርና ሽምብራ ምርቶችን መቀበል ይጀምራል። የአኩሪ አተር አቅራቢዎች አዲስ አበባ ሳሪስ፣አሶሳ፣ፓዌ፣ቡሬ፣ነቀምትና ጎንደር ቅርንጫፎች ማቅረብ የሚችሉ ሲሆን የሽምብራ አቅራቢዎች ደግሞ በአዲስ አበባ ሳሪስ፣አዳማ፣ቡሬ፣ ኮምቦልቻና ጎንደር  ማቅረብ እንደሚችሉና ምርት ገበያው በቂ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል። ይህም አርሶ አደሮችን፣አቅራቢዎችንና ላኪዎችን ተጠቃሚ ከማድረጉም በላይ ለአገሪቱ የወጪ ንግድና የውጭ ምንዛሬ ዕድገት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው የተገለጸው። አርሶ አደሮችም ጥራት ያለው ምርት አምርተው የተሻለ ዋጋ እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑና የግብይት ስርዓቱ በባንክ ላይ የተመሰረተ የገንዘብ ፍሰት በማድረግ ለየአካባቢው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ተጨማሪ መነቃቃት እንደሚፈጥር መግለጫው አመልክቷል። በአገሪቱ አኩሪ አተር በየዓመቱ ከ812 ሺሀ ኩንታል በላይ የሚመረት ሲሆን ከዚህም ውስጥ 99 በመቶው በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች ይመረታል። በ2011 በጀት አመት በአራት ወራት ውስጥ በወጪ ንግድ 5 ሺህ 24 ቶን አኩሪ አተር ለሽያጭ ውሎ 68 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ተገኝቷል። ህንድ፣ቻይና፣ሲንጋፖርና ቬትናም የኢትዮጵያን አኩሪ አተር ምርት በብዛት ከሚገዙ አገራት መካከል ናቸው። በመግለጫው እንደተመለከተው 75 ሺህ ቶን ሽምብራ ለውጭ ገበያ ቀርቦ 1 ነጥብ 7 ቢሊዬን ብር ገቢ ተገኝቷል፤ የተባባሩት አረብ ኢምሬትስ፣ኢራንና ፓኪስታን ከምርቱ ገዢዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም