የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ጥበቃ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

90
አዲስ አበባ ታህሳስ 16/2011 የማዕድና ነዳጅ ሚኒስቴር የማዕድን ፍለጋና የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦዎች ጥበቃ ለማድረግ የሚያስችል ሁለት መግባቢያ ስምምነት ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር ተፈራረመ። አንዱ የስምምነት አካል ከሱማሌ ክልል እስከ ጅቡቲ የተዘረጋውን የ800 ኪሎ ሜትር የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ በበራሪ ካሜራ (ድሮን) በታገዘ ቴክኖሎጂ የጥበቃና ክትትል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለማከናወን የሚያስችል ነው። በተመሳሳይ በነዳጅና ማዕድናት ላይ የሚያደርገውን ፍለጋ በሳይንሳዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ማከናወን እንዲቻል ነው ስምምነት የተደረገው። የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርጋቱ በወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በርካታ ማዕድናትና የነዳጅ እምቅ ሀብት አላት። ሆኖም ይህን ሀብቷን አውጥታ ለመጠቀም የቴክኖሎጂ እጥረትና የመልክዓ ምድር አቀማመጥ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሮባታል። እስካሁን የተገኙትም ቢሆን በብዙ ወጪ የተሰሩ ሲሆን ፤ ፍለጋ የተካሄደባቸው አካባቢዎች ጥቂት ናቸው። በተራራማና የውሃ አካባቢዎች ፍለጋውን በበራሪ ካሜራ (ድሮን) ታግዞ ለማከናወን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አቅም እንዳለው በመግለፁ ሁለቱም ተቋማት ለመፈራረም መቻላቸው ነው የተነገረው። የማዕድንና ነዳጅ ፍለጋ ስራ ብዙ ወጪ የሚፈልግ ከመሆኑ አኳያ ይህን ለመስራት ተቋሙ አቅም እንዳለው በመግለፁ ኃላፊነት መሰጠቱን ተናግረዋል። ጅቡቲ ድረስ ተዘርግቶ ነዳጅ የሚተላለፍበት መስመር ረጅምና ተቀጣጣይ በመሆኑ ከፍተኛ ጥበቃ ያስፈልገዋል። ከዚህ አኳያ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመሩ በቴክኖሊጂ የታገዘ ጥበቃ እንዲደረግለት ነው ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር ስምምነት የተደረሰው። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ እንደገለጹት፤ ሁለቱንም ስራዎች ለማከናወን ተቋሙ ሰፊ አቅም አለ። የጥበቃውም ሆነ የፍለጋው ስራ ዘመናዊና ውድ በሆኑ ብልጭታን የመቋቋም አቅም ባላቸው የድሮን ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ እንደሚሰራ አመልክተዋል። ከዚህ ሌላ ቴክኖሎጂው በሰው ዓይን ሊታይ የሚያዳግት በቱቦ ላይ ያለ የነዳጅ ንጥበትን በመለየት ቀድሞ ለማስተካከል እንዲቻል መረጃ በማስተላለፍ ያግዛል። የሁለቱም ስምምነት የአዋጭነት ፕሮጀክት ጥናት እየተሰራ መሆኑንም ዶክተር ጌታሁን ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም