የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ፍኖተ ካርታ ማስተግበሪያ እቅድ መተግበር ጀመረ

1339

አዲስ አበባ ታህሳስ 16/2011 የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ፍኖተ ካርታ ማስተግበሪያ እቅድን ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን አስታወቀ።

በቅርቡ ለ20 ዘርፎች የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ፍኖተ ካርታ ፀድቆ ወደ ስራ የተገባ ሲሆን ለ4ቱ የማስተግበሪያ እቅድ ተዘጋጅቶላቸዋል።

ማስተግበሪያ እቅድ ከተዘጋጀላቸው የኮንስትራክሽን፣ የስኳር፣ የቆዳ እና የመስኖ ዘርፎች ሲሆኑ በእነዚህ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ ውይይት ተደርጓል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ፍኖተ ካርታው አገሪቷ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ የምታደርገውን ጉዞ በቴክኖሎጂና ምርምር አግዞ ውጤት ለማምጣት ትልቅ ሚና ይኖረዋል።

ቴክኖሎጂን በመጠቀም ጥራት ማምጣት፣ ወጪን መቆጠብ፣ ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠርና ዘርፉ ኢኮኖሚው በሚያመነጨው ገቢ ላይ የድርሻውን እንዲወጣ ማድረግ ይቻላል ብለዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ በሚቀጥሉት ሁለት አመታት በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ሁለት ሺህ ጥቃቅንና አነስተኛ ስራ ፈጣሪዎችን በማፍራት ለ20 ሺህ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዷል።

ከዚህም 57 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት እየተሰራ ሲሆን አሁን በያዘው አካሄድ ጥሩ አፈፃፀም   ከእቅድ በላይ ገቢ መሰብሰብ እንደሚያስችላቸው ተናረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የብዙ ሃብቶች መገኛ ብትሆንም በቴክኖሎጂና ምርምር ባለመታገዟ ከግብርናም ይሁን ከማምረቻ ዘርፉ የሚገባትን ጥቅም ማግኘት ሳትችል ቀርታለች።

በአጭር ጊዜ የጤናና ግብርና ዘርፉን በቴክኖሎጂ ለማገዝ በተደረገው የድሮን ቴክኖሎጂ ጥረት ውጤት መገኘቱን የገለፁት ሚኒስትሩ ስትራቴጂ ተቀርፆለት ሲሰራ ደግሞ የበለጠ ለውጥ ያመጣል ብለዋል።

ከክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲዎችና ቴክኖሎጂን ከሚጠቀሙ የተለያዩ ዘርፎች የመጡ ተወካዮች ፍኖተ ካርታው መዘጋጀቱ በቴክኖሎጂ የታገዘ ስራን ለመስራት አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።

ሆኖም እንደየዘርፋቸውና አውዳቸው ማስተግበሪያ ሲወጣ ሊለያይ በመቻሉ ለአፈፃፀም ይቸግራል፣ ለማስፈፀም የፋይናንስ ችግር አለ፣ በግል ተግባራዊ ካደረግናቸው ፍኖተ ካርታዎች ጋር አይጋጭም ወይ የሚሉ ጥያቄና አስተያየት ሰጥተዋል።

ሚኒስቴሩ በበኩሉ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ የተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ እያንዳንዱ ተቋም በሚሰራው ስራ ቴክኖሎጂንና ምርምርን እንዴት አካቶ ይሰራል የሚለውን የሚያይ በመሆኑ ምንም ተቃርኖ እንደማይፈጥር አብራርቷል።

በሚኒስቴሩ የፖሊሲ ስርታቴጂና ፊውቸር ፕላኒንግ ዳይሬክተር አቶ ደስታ አበራ እንደገለፁት እንደየስራቸው ጠባይ መተግበሪያውን ለማውጣት በሚኒስቴሩ በኩል ስልጠናና ድጋፍ ይደረግላቸዋል።

ማስተግበሪያ እቅድ የወጣላቸው አራት ዘርፎች በዚህ ዓመት በስራቸው ላይ 10 በመቶ በቴክኖሎጂ እንዲደግፉ ተደርጎ ውጤቱም በአመቱ መጨረሻ ይገመገማል ብለዋል።

ቀሪዎቹ 16 ዘርፎችም በሚቀጥሉት ሁለት ወራት የማስተግበሪያ እቅድ ወጥቶላቸው ወደ ስራ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የሲሚኒቶ፣ የስጋ፣ የቡና፣ የመአድን እና እንስሳት ዘርፍ ፍኖተ ካርታ ከተዘጋጀላቸው መካከል ይጠቀሳሉ።

በጠቅላይ ሚኒስቴሩ የሚመራው የሳይንስ፣ ቴክኒሎጂና ኢኖቬሽን ካውንስል የተመረጡ 24 ዘርፎች ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲሰራ የቆየው ሚኒስቴሩ ለ20ቹ ማዘጋጀት ቢችልም የቀሪ 4 ዘርፎች ፍኖተ ካርታም በቅርቡ ይጠናቀቃል።