የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ፀደቀ

1719

አዲስ አበባ ታህሳስ 16/2011 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብሄራዊ የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅን በአብላጫ ድምጽ አፀደቀ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 14ኛ መደበኛ ስብሰባው በውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች እና በህግ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች በቀረበለት የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ አፅድቋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዲሞክራሲ ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራትን ለማገዝ ያስችላል የተባለው ኮሚሽኑ በአዋጅ ቁጥር 1102/2011 በአንድ ተቃውሞና በአንድ ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ፀድቋል።

በተጨማሪም ለግጭትና ቁርሾ መክንያት የሆኑ ጉዳዮችን በማጣራት ዳግም አንዳይከሰቱ በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ያመላክታል ተብሏል።

አንዳንድ የምክር ቤት አባላት “የተጣላ ማህበረተሰብ በሌለበት ማንን ከማን ለማስታረቅ ነው” የሚል ሃሳብ በመሰንዘር የኮሚሽኑ መቋቋም አስፈላጊ አይደለም የሚሉ ሀሳቦችን አንስተዋል።

ህዝብ ከህዝብ ቢጣላ እንኳን “በራሱ ሽማግሌ መርጦ ይታረቃል” በማለት “የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን መቋቋም ካለበት የተኳረፉ የፖለቲካ ድርጅቶች” የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ቢባል ይሻላልም ብለዋል።

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ አስካሁን በኅብረተሰቡ ላይ ይደርስ የነበረውን በደል እያየ እንዳላየ ሲያልፍ ነበር፤ ስለዚህ አሁን ያለፈ ስህተቱን የሚያካክስበት አጋጣሚ ነው የሚሉም አሉ።

ኮሚሽኑ ከልብ ይቅር የሚያባብል፤ የመግባባት፣ ያለፉ ሰህተቶች እንዳይደገሙ የሚከላከል ትክክለኛና ወቅቱን የጠበቀ በመሆኑ አስፈላጊ ነው ሲሉም ተደምጠዋል።

በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ “ምርምራ” የሚለው ቃል መደበኛ የምርመራ ስራ ለፖሊስ በህግ የተሰጠ ስልጣን በመሆኑ ማጣራት በሚል መቀየሩም ተገልጿል።

ኢትዮጵያውያን ያላቸውን የዳበረ የሽምግልና እና የግጭት አፈታት በማገዝ የግጭት መንስኤዎችን ይበልጥ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ አጣርቶ የመፍትሄ ሃሳብ የሚያቀርብ ኮሚሽን መሆኑም ተገልጿል።

ኮሚሽኑ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሆን አባላቱ በጠቅላይ ሚኒስስትሩ ቀርበው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነጻና ገለልተኛ መሆናቸው ተለይቶ የሚጸድቅ ይሆናል ተብሏል።

በተጨማሪም የኮሚሽኑ አባላት በየትኛውም ብሄር ስማቸው በመጥፎ የማይነሳ በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ዜጎች ስብስብ እንደሚሆን ነው የተገለፀው።