በቤንች ማጂ ዞን ሸኮ ወረዳ በነበረው ግጭት የተጠረጠሩ 23 ግለሰቦች ተያዙ - ኢዜአ አማርኛ
በቤንች ማጂ ዞን ሸኮ ወረዳ በነበረው ግጭት የተጠረጠሩ 23 ግለሰቦች ተያዙ
ሚዛን ታህሳስ 16/2011 በቤንች ማጂ ዞን ሸኮ ወረዳ ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር የተጠረጠሩ 23 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ። የዞኑ ፖሊስ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ምናሉ ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት ግለሰቦቹ ታህሳስ 10 ቀን 2011 ዓም በሸኮ ወረዳ ሽሚ አካባቢ ተከስቶ በነበረው ግጭት የተጠረጠሩ ናቸው። ከዞንነት የመዋቅር ጥያቄ ጋር በተያያዘ ተከስቶ በነበረው ግጭት ፖሊስ ጣቢያን ጨምሮ በመንግስትና በግለሰብ ቤቶችና ተሽከርካሪዎች ላይ ዝርፊያና ቃጠሎ መፈጸሙን ገልጸው ''በወቅቱ በተደረገ ሰላም የማስከበር እንቅስቃሴም የሁለት ሰዎች ህይወት አልፏል'' ብለዋል። በግጭቱ የተጠረጠሩ 23 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እየታየ እንደሚገኝ የገለጹት ዋና ኢንስፔክተር ምናሉ ከ20 በላይ የጦር መሣሪያ ማስመለስ መቻሉንም ተናግረዋል። ''በአንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎችና ግጭቱ እንዲባባስ በሚሹ አካላት የግጭቱ ምክንያት በብሔረሰቦች መካከል እንደተፈጠረ ተደርጎ የተናፈሰው መረጃ ከእውነት የራቀ ነው'' ብለዋል። በአሁኑ ወቅትም አካባቢው ወደ ሰላማዊ ሁኔታ መመለሱንና ዳግም የጸጥታ ችግር እንዳይከሰትም ህብረተሰቡን በማሳተፍ እየተሰራ መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል፡፡