የመደመር ገፀ-በረከት !

111
መሀመድ ረሻድ ጎባ (ኢዜአ) ሰላም ከሌለ የሰው ልጆች ብቻ ሳይሆኑ እንስሳትም እንደፈለጉ በልተው ጠጥተው ማደርና መንቀሳቀስ እንደማይችሉ እሙን ነው። በሰላም እጦት ምክንያት ደግሞ ሰርቶ መለወጥ፤ ወልዶ መሳምና ለወግ መዓረግ መብቃት እንደማይቻል አያጠያይቅም ፡፡ ያለ ሰላም ዲፕሎማሲና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የሚባል ነገር አይታሰበም ። በኢትዮጰያና ኤርትራ መካከል ሃያ ዓመታትን ያስቆጠረው ቅራኔ የሰላም መታጣት የሚያስከትለው ጦስ ማሳያ አድርገን ማየት እንችላለን ። የሁለቱ ሀገራት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስተጋብራቸው ተቋርጦ መቆየቱ በሁለቱም ወገን ያሉ ህዝቦችን ክፉኛ ጎድቷል፡፡ የእርስ በእርስ ግንኙነት ተቋርጧል፡፡ በሞቀ  ህይወት ውስጥ የነበረ ቤተሰብ ተበትኗል፡፡ ተለያይቷል፡፡ ይህ ደግሞ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ሞራላዊ ቀውስ አስከትሏል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ችግሩን በመፍታት ባሳዩት ቁርጠኝነት በአጭር ጊዜ ውስጥ የሀገራቱን የቀድሞ ወዳጅነት ወደ ነበረበት በመመለስ እጅግ የሚያስመሰግን ተግባር ፈጽመዋል፡፡ ለስምምነቱ እውን መሆን የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቅ ያሳዩት ቁርጠኝነት አለማድነቅም ንፉግነት ነው ፡፡ በሁለቱ አገራት መካከል የነበረው ቅራኔ በመፈታቱ የሁለቱም ሰላምና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ከመጠናከሩም ባሻገር በማህበራዊ መስኩም ተለያይተው የነበሩት  ወንድማማቾች ከዘመናት ቆይታ በኋላ መገናኘት መቻላቸው ሌላው የግንኙነቱ ገፀ በረከት አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡ በኢትዮ-ኤርትሪያ ግንኙነት መሻከር ምክንያት ለዓመታት ተጠፋፍተው የነበሩ ቤተሰቦች ሰሞኑን በባሌ ዞን ሮቤ ከተማ መገናኘታቸው ለዛሬው ጽሁፌ መነሻ አድርጌዋለሁ ። የ75 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ አቶ አብዱልቃዲር ጁንዳ የባሌ ሮቤ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ በ1970 ዎቹ ውስጥ የእናት ሀገር ጥሪ ተብሎ በሚታወቀው የደርግ የክተት ዘመቻ በለጋ ዕድሜያቸው ተይዘው ወደ ኤርትራ ለውትድርና ተግባር መሄዳቸውን ይናገራሉ፡፡ ለ17 ዓመታት በውትድርና አገራቸውን አገልግለዋል ፡፡ በኤርትራ በውትድርና ቆይታቸውም  ከአንዲት ኤርትራዊ እንስት  ጋር ተዋውቀው የጀመሩት ፍቅር ወደ ትዳር አምርቶ አምስት ልጆችን አፍርተው ነበር ። በተፈጥሮ ህግጋት ሁለቱ በህይወት ባይኖሩም  ሰሚራ፤ ኢብራሂምና ሰናይት አብዱል ቃድር ግን አሁንም በህይወት አሉ ። አቶ አብዱልቃድር ጁንዳ ከደርግ ውድቀት በኋላም እዛው ኤርትራ ውስጥ  ከነቤተሰቦቻቸው በከረን ከተማ እጅግ በጣም ጥሩ የሚባል ኑሮ ይመሩ እንደነበር ይገልፃሉ ። አገር አማን ነው ብለው ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ጠይቀው ለመመለስ ወደ ትውልድ አገራቸው ኢትዮጵያ በመጡበት በ1990ዎቹ መጀመሪያ በሁለቱ አገራት መካከል ጦርነት ተጀመረና ከሚወዱዋቸው ቤተሰቦች ተለይተው እንደወጡ ይቀራሉ ። ከውድ ባለቤታቸውና ከአብራካቸው ክፋዮች ለመገናኘት 20 ዓመታትን በናፍቆት ማንባት ግድ ሆኖባቸው ቆይቷል ። ”አንድ ቀን የምወዳቸው ቤተሰቦቼን ዳግም በአይነ ስጋ እንደማገኘቸው ግን ውስጤ ይነግረኝ ነበር ። ለዚህ ነው ተስፋ ሳልቆርጥ ዓመታትን በትዕግስት ያሳለፍኩት ” ይላሉ ። አቶ አብዱልቃድር የተመኙት አልቀረም  ። ጊዜውን ጠብቆ የዛሬ ሁለት  ሳምንት ከሁለት ልጆቻቸው ጋር በአካል ተገናኝተው ተቃቀፉና እንደያኔው የናፍቆት ሳይሆን የደስታ እንባ ፊታቸውን አረጠበው ። ሰሚራ የአቶ አብዱልቃድር የመጀመሪያ ልጅ ናት ። ወላጅ አባቷ ሲለዩዋት የ10 ዓመት ልጅ ነበረች ። ታናሽ ወንድሟን አስከትላ አባቷን ፍለጋ ወደ ኢትዮጵያ ያደረገችው ጉዞ መሳካቱን ፍንድቅድቅ ብላ ትገልፀዋለች ። አባታችን የት ሄደ ? እንደወጣስ ለምን አልተመለሰም ? የትውልድ አገሩና አካባቢውስ ምን ተብሎ ይጠራል ? የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎች እየመላለሰች እናትዋን መወትወትዋ ዛሬ አባትዋን ለማግኘት እንደጠቀማት ትገልፃለች ። ” አባትሽ ኦሮሞ ነው ። ተወልዶ ያደገውና የቤተሰቡ አድራሻ ባሌ ይባላል በማለት እናቴ የነገረችኝን በልጅነት ልቦናዬ ታትሞ በመዝለቁ ዛሬ ላይ ከአባቴ ጋር እንድሳሳም አድርጎኛል ” ትላለች- ሰሚራ ። ”ከእናቴ የተቀበልኩትን አድራሻ በመጠቀም አዲስ አባባ የምትኖረው “ሃና” በምትባል የፌስ ቡክ ጓደኛዬ በኩል  ታምራት  የሚባል የባሌ ሰው ስለተባበረን ህልማችን ማሳካት ችለናል” ትላለች ። ሰሚራ እንዳለችው አባቴን ለመጀመሪያ ጊዜ በስልክ ድምፁን ስሰማ እሱ ስለመሆኑ ምንም አልተጠራጠርኩኝም፡፡ አባቴን ዳግም በማግኘቴም በቃላት ሊገለጽ የማይችል ደስታ ተሰምቶኛል ትላለች፡፡ ሰሚራ ማህበራዊ ሚዲያ ለበጎ ተግባር ከተጠቀምንበት ትልቅ መሳሪያ መሆኑን ጭምር ተገንዝቤያለሁ ትላለች ። አባታቸው ከቤተሰብ መለየታቸው ኩፍኛ እንደጎዳት ሰሚራ ትናገራለች ። በቤተሰቦቿ ላይ የመበታተን አደጋ ተጋርጦበት ነበር ። እሷም በ14 ዓመቷ ወደ ሱዳን ለመሰደድ ግድ ብላቷል ። ዛሬ ላይ በ30ዎቹ የእድሜ ክልል መጀመሪያ የምትገኘው ሰሚራ የስደት ህይወቷን ባስታወሰች ቁጥር እንባ ይተናነቃታል ። ውጤቱም የጦርነቱ አስከፊነት ያመጣው ጣጣ መሆኑን ትገነዘባለች ። በኤርትራ ከረን ከተማ የብስክሌት ስፖርተኛው ኢብራሂም ደግሞ የአቶ አብዱቃድር ሁለተኛ ልጅ ነው ። ከእህቱ ሰሚራ ጋር በመሆን አባቱን ለማግኘት ወደ ኢትዮጵያ ያደረገው ጉዞ ውጤታማ በማለት ይገልፀዋል ። ሰሚራና ወንድሟ ኢብራሂም ኢትዮጵያና ኤርትራ ከሁለት አስርታ ዓመታት አለመግባባት በኋላ ሰላም ማውረዳቸው ከማንም በላይ ተጠቃሚዎች እንዳደረጋቸው ይናገራሉ ። በሁለቱም አገራትና ህዝቦቻቸው መሀከል ተጋርዶ የነበረው ጥቁር መጋረጃ በመበጣጠሱም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና  የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቅን ያመሰግናሉ ። የእናታቸውን ምርቃት ተቀብለው  አባታቸውን ፍለጋ ወደ ሌላኛው ግን ደግሞ ከአሁን በፊት ወደማያውቁት አገራቸው የመጡት ወንድምና እህት በለስ ቀንቷቸው ያሰቡት በመሳካቱ ”ሁለተኛ የተወለድን ያክል አድርገን እንቆጥረዋለን” ብለዋል ። ወንድምና እህት እራሳቸውን እድለኛ አድርገው ያዩት አንድ መልካም አጋጣሚም ተፈጥሮላቸዋል ። እናታቸውም ሆኑ አባታቸው አንዱ ሌላውን በተስፋ ሲጠብቁ ሌላ ትዳር አልመሰረቱም ። እናማ አባታቸውን ይዘው ወደ ከረን ለመመለስና እንደድሮው ትልቁ ቤተሰብ በአንድ ጣሪያ ስር ለመሰባሰብ አቅደዋል። አቶ አብዱልቃድር ጁንዳ በበኩላቸው ሊገልፁት የማይችሉት ደስታ እንደተሰማቸው ይናገራሉ ። ህይወት ያለ ልባዊ አጋርና ያለ አብራኬ ክፋዮች እጅግ ከባድ ነበር ። አሁን ግን በተፈጠረው ሰላም የኔም ውስጣዊ ሰላም ተመልሶልኛል ብለዋል ። ልጆቿን በታላቅ ሃላፊነት ለማሳደግ ከበቃችው ባለቤቴ ጋር ለመገናኘት  ወደ ኤርትራ ከረን ከተማ ለመሄድ ጓጉቻለሁ ሲሉም  ተናግረዋል፡፡ ለሆነው ነገር ሁሉ ፈጣሪን ያመሰገኑት አቶ አብዱልቃደር የጥላቻ ግንብ ፈርሶ የፍቅር ድልድይ እንዲገነባ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድንና ለኤትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል ። አቶ አብዱልቃዲር ጁንዳ “ከባሌ እስከ ከረን” የዘለቀውን በውጣ ውረድ የተሞላ ህይወታቸውን ሲቋጩ "ያለፈው አልፏል ይህ በቋንቋ፣ባህል፣ አኗኗርና መሰል ጠንካራ ገመድ የተሳሰረ ህዝብ የፍቅር አንድነትና የመደመር ፍልስፍናን ተላብሶ ለወደፊቱ የጋራ ብልፅግና  ሊሰራ ይገባል" የሚል መልእክት አስተላልፈዋል ፡፡ ያለፈውን ቁርሾ በመርሳት በአገሪቱ ብሎም በቀጠናው አስተማማኝ ሰላም በማስፈን የተጀመረውን አገራዊ የለውጥ ሂደትና አብሮ የማደግ እሳቤ ከዳር እንዲደርስ ሁላችንም ሀላፊነታችንን እንወጣ ፡፡  ሰላም ለሀገራችን !          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም