በወላይታ ሶዶ የቤንዝን እጥረት የታክሲ አገልግሎትን አስተጓጉሏል

58
ሶዶ ታህሳስ 15/2011 በወላይታ ሶደ የቤንዝን እጥረት የታክሲ አገልግሎት መስተጓጎልና ከታሪፍ በላይ ክፍያን ማስከተሉን  አስተያየታቸውን የሰጡ  ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ በከተማዋ የኪዳነ ምህረት ቀበሌ ነዋሪ  አቶ ከበደ ኃይሌ እንዳሉት ከቤንዚን እጥረት ጋር ተያይዞ ካለፉት ሁለት ወራት ጀምሮ በጃጆች ጨምሮ ሌሎችም ታክሲዎች  በአግባቡ እየሰሩ አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት የታክሲ አገልግሎቱ በመስተጓጎሉና ከታሪፍ በላይ ክፍያ መጠየቁ እንቅስቃሴያቸውን በመገደብ  እንደተቸገሩ አመልክተዋል፡፡ በተለምዶ ሰላሳ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ሁለት ባጃጅ በመያዝ ዘወትር ወደ ስራ እንደሚሄዱ የተናገሩት ወይዘሮ ፈለቀች ዳንሳ ሁለት ብር ይከፈልበት የነበረው የባጃጅ ትራንስፖርት በእጥፍ እንደጨመረ ጠቁመዋል፡፡ ቤንዚን በእጥፍ እየገዛን ነው የምንሰራው የሚል ምላሽ ከአሽከርካሪዎች እንደሚሰጣቸውና የተጠየቁትን ካልከፈሉ መሳፈር እንደማይችሉ  ገልጸዋል፡፡ የሶዶ ከተማ ታክሲ ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ዘርሁን ስምኦን ከህዝቡ የሚነሳው ቅሬታ ትክክል መሆኑን ገልጸው ካለፈው ነሐሴ ወር አጋማሽ ጀምሮ የገጠመቸው የቤንዚን እጥረት ታክሲዎች ስራቸዉን በአግባቡ እንዳይወጡ ማድረጉን አመልክተዋል፡፡ በከተማው ውስጥ የሚገኙ ማደያዎች የአገልግሎት አሰጣጥ ፍትሃዊነት ጉድለት ሌላኛው ችግር እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ በማህበሩ የታቀፉ ከ600 በላይ ባለሶስት እግር የከተማ ታክሲ አሽከርካሪዎች እንዳሉ አመልክተው በተፈጠረው ችግር ስራቸውን በአግባቡ ማከናወን እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡ ሊትሩን ቤንዝን በውድ ዋጋ ስለሚገዙ የትራንስፓርት ዋጋ ለመጨመር እንደሚገደዱና በበችግሩ ዙሪያ ማህበሩ  ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር ተደጋጋሚ ውይይት ቢያካሂድም መፍትሄ እንዳልተሰጠ አስረድተዋል፡፡ የከተማው አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሰለ ሶርሳ የነዋሪዎች ቅሬታ ትክክል መሆኑን አምነው የፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን እንዲሁም ወጥነት የሌለው አቅርቦት እጥረት ማስከተሉን ገልጸዋል፡፡ ከአጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች በህገ-ወጥ መልክ በበርሜልና በጄሪካን እየቀዱ የሚያሸሹ ነጋዴዎችና በከተማው ውስጥም  ቤንዚን በማመላለስ የተሰማሩ ህገ-ወጦች መበራከት ሌላው ችግር ነው ሲሉ አቶ መሰለ ተናግረዋል ፡፡ "ችግሩን ለመፍታት ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን በተወሰደው እርምጃ ባለፈው ሳምንት ከአንድ ሺህ 700 ሊትር በላይ ቤንዚን በህገወጥ መንገድ ተደብቆ በመገኘቱ ተይዞ ለባጃጅ አሽከርካሪዎች መከፋፈሉንና ድርጊቱን የፈጸመው ግለሰብን ለህግ ለማቅረብ እየተሰራ ነው" ብለዋል፡፡ በአንዳንድ የቤንዚን ማዳያዎች  የሚስተዋለውን ፍትሐዊ የአገልግሎት አሳጣጥ ጉድለት ለማረም ክትትል እያደረጉ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ በወላይታ ሶዶ ከተማ ዘጠኝ  የቤንዚን ማደያዎች እንደሚገኙ ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም