በክልሉ በጣዕምና በጥራታቸው የተመረጡ የቡና ዝርያዎች ለዓለም ገበያ ሊቀርቡ ነው

1015

ጎንደር ታህሳስ 15/2011 በአማራ ክልል በጣዕምና በጥራታቸው የአካባቢ መለያ መጠሪያ የተሰጣቸው የቡና ዝርያዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ገበያ ሊቀርቡ ነው።

የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ እንዳስታወቀው ዝርያዎቹን ለገበያው ለማቅረብ የልየታ ሥራ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ተከናውኗል።

በክልሉ አራት ዞኖች ከ400ሺህ ኩንታል በላይ ለገበያው የሚቀርብበት እምቅ ሀብት መኖሩም በጥናት ተለይቷል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በጎንደር ከተማ ለባለ ድርሻ አካላት ያዘጋጀው የትውውቅ ፕሮግራም ትናንት ተካሂዷል፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ዮሐንስ አፈወርቅ ለኢዜአ እንደገለጹት በባህርዳርና አካባቢው ፣ በምስራቅና ምእራብ ጎጃም እንዲሁም በአዊ ዞኖች በጣዕምና በጥራታቸው የተለዩ የቡና ዝርያዎች የአካባቢ ስያሜ ተሰጥቷቸዋል፡፡

መለያ ከተሰጣቸው የቡና ናሙናዎች  በዚህ ዓመት 200 ኩንታል ቡና ውጭ ገበያ ላይ ተቀባይነት አግኝቷል ብለዋል፡፡

ዝርያዎቹን ለዓለም ገበያ ለማቅረብ የቡና ዩኒየን ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን  አቶ ዮሐንስ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የግብይትና የመጋዘን አገልግሎት ደህንነትና ቁጥጥር የስራ ክፍል ኃላፊ አቶ በረከት መሰረት በበኩላቸው በክልሉ ያለውን ቡና ጥቅም ላይ ለማዋል ጥናት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዚህም የምርቱን መጠን ከመለየት ጀምሮ ጣዕምና ባህሪውን  በመለየት ቡና አምራቾች ግብይት የሚፈጽሙበት አሰራር በቅርቡ እንደሚዘረጋ አስረድተዋል፡፡

በክልሉ በጣዕሙም ሆነ በጥራቱ በጥናት የተረጋገጠ የቡና ዝርያ መኖሩን አረጋግጠናል ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የስልጠናና ሰርተፊኬሽን ክፍል ኃላፊ አቶ ወርቅነህ ሙላት ናቸው፡፡

በተለይም በምዕራብ ጎጃም ዞን ከፍተኛ የቡና ምርት እንደሚገኝና በክልሉ እስከ 400ሺህ ኩንታል ሊመረት እንደሚችል መረጋገጡን  ገልጸዋል፡፡

የአዊ ዞን ንግድና ኢንዱስትሪ መምሪያ የግብይት ባለሙያ አቶ ተስፋዬ እንየው በበኩላቸው የአዊ ቡና የአካባቢ መለያ ማግኘቱን ተናግረዋል።

በዞኑ ሰባት ወረዳዎችም ቡና በስፋት ይመረታል ብለዋል፡፡

አምራቹ ቡናውን ለገበያ በማቅረብ በዋጋው ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባዘጋጀው የትውውቅ ፕሮግራም ላይ ከምስራቅና ምዕራብ ጎጃም፣ ከአዊ፣ ከማዕከላዊና ምእራብ ጎንደር ዞኖች የተውጣጡ በግብይት እሴት ሰንሰለት ውስጥ ተሳትፎ ያላቸው የመንግሥትና የግብይት ተዋናዮች ተሳትፈዋል፡፡

ምርት ገበያው በታህሳስና ጥር ወራት ሽንብራ፣ አኩሪ አተር፣ ኑግና ባቄላን ወደ ግብይት ሰንሰለት እንደሚያስገባ አስታውቋል፡፡