ለተፈናቃዮች ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ተደረገ

1597

ነቀምቴ ታህሳስ 15/2011 ከቤንሻጉል ጉሙዝ ክልል ካማሽ ዞንና አዋሳኝ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ ወገኖች  ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን  ብር የሚገመት ድጋፍ ተደረገ።

በምሥራቅ ወለጋ ዞን ለተጠለሉት ወገኖች ድጋፉን ያደረጉት በአዲስ አበባ የቦሌ ክፍለ  ከተማ ነዋሪዎችና የጅማ ዞን ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ጽህፈት ቤት ናቸው።

ነዋሪዎቹ ሁለት ሚሊዮን ብር የሚገመት የምግብ፣  አልባሳትና ቁሳቁስ ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን፣ጽህፈት ቤቱ በበኩሉ ከ200 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው ተመሳሳይ ድጋፍ አድርጓል።

የቦሌ ክፍለ ከተማ የዕርዳታ አሰባሳቢ ቡድን አስተባባሪ አቶ ፍቅሩ በየነ ባለፈው ቅዳሜ ድጋፉን ለዞኑ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳርጌ ጉደታአስረክበዋል።

ድጋፉ ከመንግሥት ሠራተኞች፣ወጣቶች፣ሴቶችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች መሰባሰቡን ገልጸዋል።

ድጋፉ ዱቄት፣ ስኳር፣ ፓስታና ማካሮኒ ማካተቱን አስታውቀዋል ።

የዞኑ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳርጌ  በዚሁ ጊዜ  እንዳሉት ዜጎች  ለተፈናቃዮች ላደረጉት ድጋፍም አመስግነዋል።