አብዛኛዎቹ ኢንዱስትሪዎች የአካባቢ ደህንነት መስፈርት ሳያሟሉ እያመረቱ ነው

2345

አዳማ ታህሳስ 15/2011 አብዛኛዎቹ አምራች ኢንዱስትሪዎችና ተቋማት በህግ የተቀመጣውን የአካባቢ ደህንነት መስፈርት ሳያሟሉ እያመረቱ እንደሚገኙ በተደረገው ቁጥጥር መረጋገጡን የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከአምራች ድርጅቶችና ተቋማት የተወጣጡ ባለድርሻ አካላትን ፣ ከፌዴራልና ከክልል የሴክተሩ መስሪያ ቤቶች ጋር በአዳማ እየመከረ ነው።

በኮሚሽኑ የህግ ተካባሪነት ዳይሬክተር ጄኔራልና በምክክር መድረኩ  የቁጥጥር ግኝት ውጤት ያቀረቡት አቶ መሪህ ወንድማገኝ እንዳሉት  ባለፈው የበጀት ዓመት በፌዴራል ደረጃ ባሉት 50 ኢንዱስትሪዎችና  በክልሎች ባሉት 29 ሺህ 576 በሚሆኑት የማምረቻ  ተቋማት ላይ ቁጥጥር ተደርጓል፡፡

በዚህም አብዛኛዎቹ  ለአካባቢ ብክለት በተጋለጠ መልኩ እያመረቱ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ይህ ችግር  የአካባቢ ብክለት፣  በዜጎች ደህንነትና ጤንነት ላይ አደጋ እያስከተሉ በመሆኑ 55 ፋብሪካዎችና አምራች ተቋማት እንዲዘጉ መደረጋቸውንም ጠቅሰዋል።

1ሺህ 463 በሚሆኑት ላይ የመጀመሪያና የመጨረሻ  ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ጠቅሰው ” አሁን የምንወስደው እርምጃ በተቋማቱ ላይ የታዩትን ለውጦችና ጉድለቶች በመለየት ነው” ብለዋል።

ቁጥጥር ከተደረገባቸው 54 የአበባ እርሻ ድርጅቶች ውስጥ ከሶስቱ በስተቀር በሁሉም በአካባቢ ደህንነት ላይ ከፍተኛ  ችግር እንደሚያስከትሉ  አመልክተዋል።

የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፈሰር ፍቃዱ በየነ በበኩላቸው  ወደ አካባቢ አየር በሚለቀቀው ሙቀት አማቂ ጋሶች ምክንያት የብዝህ ሕይወት መመናመን ፣ የመሬት መራቆትና የደን ውድመት በማስከተል የሰው ልጅ የመኖር ህልውናውን እየተፈታተኑ መሆኑን ገልጸዋል።

“ዓመታዊ የኢንዱስትሪ ዕድገት እስከ 14 በመቶ  ለማስመዝገብ ተጨማሪ የተፈጥሮ ሀብት ፍላጎት፣የኃይል  አቅርቦት፣መሰረተ ልማት ዝርጋታና የትርንስፖርት አገልግሎት ይጠይቃል” ብለዋል፡፡

ይህን በአግባቡ መያዝና ማልማት ካልተቻለ ከፍተኛ የአካባቢ ብክለት እንደሚያስከትል አመልክተዋል፡፡

ሀገሪቱ እያካሄደች ያለው ልማትና የኢንዱስትሪ ማስፋፋት ሥራ አካባቢያዊ ዘላቂነትና ማህበራዊ ፍትህ የሚያረጋግጡ ሆኖ እንዲቀጥሉ ሁሉም  በቅንጅት መረባረብ እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

የሚከናወኑ  የልማትና የኢንቨስትመንት ሥራዎችን በአግባቡ ማጤን ካልተቻለ ፈጣን የሆነ የኢንዱስትሪ እድገት ከዚህን በፊት ያልተከሰተ አዲስ ጫና በተፈጥሮ ሀብትና አካባቢ ላይ እንደሚፈጥር ኮሚሽነሩ  ተናግረዋል።

“የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር፣ፈጣን የከተሞች መስፋፋትና የህዝብ ቁጥር መጨመር፣የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ኋላቀሪነት ይህን ሊሸከም የሚችል መሰረተ ልማትና ቴክኖሎጂዎች የሉም “ብለዋል።

በክልሉ በልማት ላይ ከሚገኙት የኢንቨስትመንት ተቋማት ውስጥ የአበባ ልማት እርሻዎች፣የቆዳ ፣ጨርቃ ጨርቅና ብረታ ብረት ኢንዱስትሪዎች ከመሬት አጠቃቀም ፣የፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ችግር እንዳሉባቸው የገለጸው ደግሞ  የኦሮሚያ አካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ነው፡፡

በዚህም ከአስር  በላይ የቆዳ፣ብረታ ብረት፣የሶዳ አሽና ሌሎች ኢንዱስትሪዎች በጥናት ተለይተው በተሰጣቸው ማስጠንቀቂያ ሊታረሙ ባለመቻላችው መዘጋታቸውን በባለስልጣኑ የአካባቢ ቁጥጥር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ስንታየው በፍቃዱ አስታውቀዋል።

ኮሚሽኑ ለሶስት ቀናት ያዘጋጀው የምክክር መድረክ ዓላማ ባለሃብቶችና መንግስት ተቀናጅተው ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልክ አካባቢያዊና ማህበራዊ ኃላፊነታችን በጋራ ለመወጣት የሚያግዝ  አቅጣጫ በማስቀመጥ ተግባራዊ ለማድረግ እንደሆነ ተመልክቷል።