የግል ተቋማት በውስጣቸው ያለውን የሙስና ተግባር በራስ አቅም የመከላከል አቅም መፍጠር ይጠበቅባቸዋል ተባለ

962

አዲስ አበባ ታህሳስ 15/2011 የግሉ ዘርፍ ተቋማት በውስጣቸው ያለውን የሙስናና ብልሹ አሰራር በራስ አቅም ለመከላከል የሚያስችላቸውን አቅም መፍጠር እንዳለባቸው የፌዴራል የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ገለፀ።

በኢትዮጵያ የተለያየ ዘርፍ በተሰማሩ የግል ተቋማት ውስጥ በርካታ የሙስናና ብልሹ አሰራር እንዳለ በጥናት መረጋገጡንም ኮሚሽኑ አስታውቋል።

የግል ተቋማት ጠንካራ ተወዳዳሪ ሆነው ለአገራዊው የምጣኔ ኃብት ዕድገት የበኩላቸውን ገንቢ ሚና መጫወት ይችሉ ዘንድ ሙስናንና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል የሚያስችል ብቃት መፍጠር ይጠበቅባቸዋል።

በግሉ ዘርፍ የሚፈፀሙ የሙስና ተግባራትን በተቋማቱ የራስ አቅም መከላከል እንዲቻል “የግል ዘርፍ የሥነ-ምግባር ግንባታ ተቋማዊ የሙስና ስጋት አስተዳደር” በሚል ኮሚሽኑ ያተዘጋጀውን ሰነድ ለማጎልበት ያለመ ውይይት ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ተካሂዷል።

በዚህ ጊዜ የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ወዶ አጦ እንደገለጹት የግል ተቋማት ከሚያንቀሳቅሱት የአገርና የህዝብ ኃብት ግዙፍነት አንፃር በውስጣቸው የሚፈፀሙትን የሙስናና ብልሹ አሰራር በራሳቸው አቅም መቅረፍና ማስወገድ ይኖርባቸዋል።

በግሉ ዘርፍ የሚኖር ሙስናን የመከላከል አቅም አገሪቷ ከግብርና ወደኢንዱስትሪ ክፍለ ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የምታደርገውን ጥረት ለማፋጠን እንደሚያግዝ ነው ምክትል ኮሚሽነሩ የገለፁት።

በተለያዩ የልማት ዘርፎች ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ፣ ጥራትና አቅርቦትን  ለማሻሻልና  ፍትሃዊ የነፃ ውድድር ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ለማሳካትም  መሳሪያ ይሆናል ብለዋል።

ኮሚሽኑ ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ በተሻሻለው አዋጁ መሰረት በግል ተቋማት ላይ የሚስተዋሉ የሙስና ችግሮችን ለመቅረፍ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ ረቂቅ መመሪያውን ያብራሩት የኮሚሽኑ የሙስና መከላከል ዳይሬክተር ቡድን መሪ አቶ ተስፋዬ በቀለ በበኩላቸው በግሉ ተቋማት ላይ በተካሄደው የዳሰሳ ጥናት በበርካታ መስኮች የሙስናና ብልሹ አሰራር መኖራቸውን ተለይቷል።

ሙስናና ብልሹ አሰራሮች አሉባቸው ተብለው ከተለዩት ተቋማት መካከል የግል ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ ኮንስትራክሽን ድርጅቶች፣ ባንኮችና ኢንሹራን ኩባንያዎች ይገኙበታል።

በመሆኑም ረቂቅ መመሪያው ፀድቆ ሲወጣ ኮሚሽኑ ድጋፍ በማድረግ የግል ተቋማት በራሳቸው አቅም ሙስናና በልሹ አሰራርን ለመታገልና ለመከላከል ያስችላቸዋል ሲሉ ነው አቶ ተስፋዬ የገለፁት።

ይህም በአገሪቱ እያደገ የመጣውን የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ለማፋጠን፣ የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን ከብልሹ አሰራር የፀዳ በማድረግ አገራዊ እድገቱን ለማቀላጠፍ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

አቶ ተስፋዬ ከበደ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ኮሚሽኑ ፍትሃዊ የንግድ ውድድር ለማስፈን የሚያደርገው እንቅስቃሴ ከንግድ ውድድርና ሸማቾች ባለስልጣን ተግባር ጋር እንዳይደራረብ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

አቶ ተክሉ ወዳጄ የተባሉ አስተያየት ሰጨ በበኩላቸው ኮሚሽኑ በመንግስትና በልማት ድርጅቶች ላይ ካመጣው ውጤት የላቀ እንዲመዘገብ ከግል ተቋማት ጋር ያሉትን አሰራሮች በጥልቀት ማስገንዘብ እንደሚኖርበት ገልፀዋል።

የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን በመንግስትና በልማት ድርጅቶች ላይ የነበረው መብት በግል ተቋማትም ላይ እንዲሆን በ2007 ዓ.ም በተሻሻለው በአዋጅ ቁጥር 883/2007 የግል ተቋማት የሙስናና ብልሹ አሰራር የመከላከል ሥራ እንዲሰራ ስልጣን ተሰጥቶታል።

በአዋጁ መሰረት የግል ተቋማት ማለት በማንኛውም የሕግ አግባብ ለትርፍ ዓላማ የተቋቋመ ወይም ለትርፍ ዓላማ ያልተቋቋመ የግል ዘርፍ ሲሆን የህዝባዊ ድርጅቶችንም ይጨምራል።

በኢትዮጵያ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተስተዋለ ያለው ከፍተኛ የሙስናና ብልሹ አሰራር የአገሪቱን ምጣኔ ኃብት ክፉኛ አየጎዳው መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ።