ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መልዕክት አስተላለፉ

123
አዲስ አበባ ታህሳስ 15/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ በተፈጠረው ጊዜያዊ ችግር ተማሪዎች ሳይደናገጡ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ መልዕክት አስተላለፉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስልክ ለተማሪዎቹ ባስተላለፉት መልዕክት፤ፍሬ በሌለው ምክንያት ወንድም ወንድሙን በመግፋት ለውጡን ወደ ኋላ ለመጎተት እየተሞከረ መሆኑን ገልጸዋል። "አብዛኛው የክፉ ሃሳብ ፍላጎት ባይሳካም ተማሪዎች ያጋጠማችሁንና ያደረባችሁን ጉዳት ተረድቻለሁም" ብለዋል። "ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ደጅ አድራችኋል፣ ተጎሳቁላችኋል፣ ተርባችኋል፣ ቁር መቷችኋል" ያሉት ዶክተር አብይ ተማሪዎቹ ለኢትዮጵያ አንድነት መስዋትነት እንደከፈሉ ቆጥረው ለአንድነትና ሰላም ቁርጠኛ አቋም እንዲወስዱ ጠይቀዋል። "ብሶታችሁ ይሰማኛል፤ እኔም እጋራዋለሁ፤ እኔም እንደ እናንተ አይነት ችግር ያጋጥመኛል" በማለት፣ ባሉበት ሆነው በትግስት በመጠበቅ ለሁሉም ትምህርት የሚሆን ተግባር እንዲፈጽሙ አስገንዝበዋቸዋል። የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የብሩህ አዕምሮ ባለቤት መሆኑን ገልጸው፤ ተማሪዎቹም ያጋጠማቸውን ፈተና ለማለፍ ብሩህ አዕምሯቸውን መጠቀም እንዳለባቸው ተናግረዋል። ጉንዳን መጥፎ ወቅቶችን ለማለፍ ክረምት ሳይገባ በትብብር ምግቡን እንደሚያዘጋጅ ሁሉ፣ ተማሪዎችም ወቅታዊ ችግሮችን ለመሻገር የጉንዳንን መንገድ መከተል እንጂ የመንጋ ወሮ በላ አንበጣ ስልት መከተል እንደሌለባቸው መክረዋል። ከዓመታት በፊት መለገስ እንጂ መለመን የማታውቀው ሶሪያ በውስጣዊ ቸግሮቿ ምክንያት ዛሬ ዜጎች ኢትዮጵያ ድረስ ለልመና መምጣታቸውን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ተማሪዎች የኢትዮጵያን ወቅታዊ ችግር በማገናዘብና መረዳት የመፍትሄ አካል እንዲሆኑ ጠይቀዋል። እባብ መናደፍ ባህሪው መሆኑን ገልጸው፤ ''እኛ ግን ለእባብ አስተሳስብ ያላቸው ገፊ አካላት እባብ በመሆን ሳይሆን የሰው አዕምሮ በመጠቀም ልቀን ማላቅ፣ መርዙን ማስተፋት ይገባናል'' ብለዋል። ተማሪዎቹ አሁን ያሉበትም ሆነ እንሂድ የሚሉበት ቦታ አገራቸው መሆኑን ገልጸውላቸዋል። በተለይ አማራና ኦሮሞ የተሳሰረና የተቀላቀለ ነው ያሉት ዶክተር አብይ፣ አዋጪው ጉዳይ በማይመች ሁኔታም ቢሆን የገጠመን ፈተና በመቋቋም ህዝቡ አንድና የተዋሀደ ሆኖ አገሪቷን አንድ እንዲያደርጋት ልብ ለልብ በመደማመጥ በቆራጥነት ችግሩን በትዕግስት ማለፍ ይጠይቃል ብለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የአካባቢው ሽማግሌዎችና አባ ገዳዎች ለተማሪዎቹ ምክር በመለገስ፣ ተማሪዎቹ ያጋጠማቸውን ችግር እንደወላጅም ሆነው በጋራ እንደሚፈቱላቸው በመግለጽ ያለምንም ስጋት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም