አርሶ አደሮች ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂን የመጠቀም ባህል እያደገ መጥቷል ፡-የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ

195
አዲስ አበባ ታህሳስ 15/2011 በአሮሚያ ክልል ያለው የምርትና ምርታማነት ዕድገት አርሶ አደሮች ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂን የመጠቀም ባህል እያደገ በመምጣቱ እንደሆነ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። የቅድመ ምርት ትንበያ እንደሚያሳየውም በክልሉ 167 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን በአሁኑ ወቅት እየተሰበሰበ ካለው  ምርት አኳያ ተቀራራቢ ውጤት ይገኛል ተብሎ ተገምቷል። የክልሉ ግብርና ቢሮ የሰብል ልማትና የዕፅዋት ዳይሬክተር አቶ ደጀኔ ኢርጳ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በክልሉ ያሉ አርሶ አደሮች ዘመናዊ የግብርና  ቴክኖሎጂን በመጠቀማቸው በየዓመቱ ያለው ምርታማነት እያደገ መጥቷል። የአርሶ አደሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የመጠቀም ባህል እየጨመረ መምጣቱ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አንጻር ትልቅ ጥቅም እንዳለውም ጠቁመዋል።  ግብርናን ለማዘመን በኩታ ገጠም መዝራትና በጥሩ ተሞክሮ የተገኘ ውጤትን ወደ ሌሎች አካባቢዎች የማስፋት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል። በሌሎች አካባቢዎች ምርትን በኮምባይነር እና በሌሎች ዘመናዊ መሳሪዎች የመሰብሰብ  ሁኔታ እየተስፋፋ የመጣ ሲሆን ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ደግሞ በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ በቆሎን በኮምባይነር መሰብሰብ እንደሚጀመር አመልክተዋል። "አጠቃላይ ግብርናን የማዘመኑ ሁኔታ በዘልማድ ከሚሰሩ ወደ ማካናይዜሽን ለመለወጥ መዋቅር ተዘርግቷል" ብለዋል። አርሶ አደሮችን በማደራጀት ኮምባይነሮችን እንዲጠቀሙ ከማድረግ በተጨማሪ አቅም ያላቸው ኮምባይነር ገዝተው ለሌሎች በማከራየት በምርት አሰባሰብ ሂደት የሚባክን ምርት ለመቀነስ መሰራቱን ተናግረዋል። በ2010/11 የምርት ዘመን በክልሉ 5 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች የተሸፈነ ሲሆን 167 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። በአሁኑ ወቅት በአራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ያለ ምርት የተሰበሰበ ሲሆን 34 ሚሊዮን ኩንታል ወደ ጎተራ እንደገባ ያስረዱት አቶ ደጀኔ በዘር ከተሸፈነው መሬት ውስጥ 70 በመቶ ምርት መሰብሰቡን ተናግረዋል። በሌላ በኩል አርሶ አደሮች ለገበያ የሚሆን ምርቶችን እንዲያመርት የሚያበረታቱ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑም የጠቆሙት አቶ ደጀኔ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግም በተያዘው ዓመት በኀብረት ስራ ዩኒየኖች አማካይነት የገበያ ትስስር ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም