በቻይና በተካሄደ የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸነፉ

811

አዲስ አበባ ታህሳስ 15/2011 በቻይና ሃይናንና ጉጂያን በተካሄደ ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸነፉ።

በሃይናን ሃንዡ በተካሄደው ውድድር በወንዶች አትሌት ማዘንጊያ አያሌው በ2 ሰአት ከ 24 ደቂቃ ከ 47 ሴኮንድ በአንደኝነት ሲያጠናቅቅ አትሌት ደረጀ ኡርጌቻ ደግሞ በ2 ሰአት ከ 27 ደቂቃ ከ51 ሴኮንድ ሶስተኛ በመሆን አጠናቋል።

ኬንያዊው አትሌት ዲክሰን ኪፕቶ ሁለተኛ በመሆን ውድድሩን ፈፅሟል።

በሴቶች አትሌት ፀሐይነሽ ፃሌ በ2 ሰአት ከ50 ደቂቃ ከ36 ሴኮንድ አንደኛ ሆናለች። አትሌቷ ውድድሩን አንደኛ ሆና ብታጠናቅቅም የገባችበት ሰዓት ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚደረጉ የማራቶን ውድድሮች በአንፃራዊነት የዘገየ ሆኖ ተመዝግቧል።

በማራቶን ውድድሮች በአማካይ ሴቶች የሚገቡበት ሰአት 2 ሰአት ከ22 ደቂቃ እስከ 2 ሰአት ከ45 ደቂቃ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በሌላ በኩል በጉጂያን ግዛት በተካሄደው የፉዦ ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድር በወንዶች አትሌት ገዜ ታደሰ በ2 ሰአት ከ15 ደቂቃ ከ23 ሴኮንድ አሸናፊ ሆኗል።

አትሌት ወርቁ አህመድ ደግሞ በ2 ሰአት ከ16 ደቂቃ ከ16 ሴኮንድ በሶስተኛነት ማጠናቀቁን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታዎች በቻይና በሚደረጉ የማራቶን ውድድሮች በአሸናፊነት በመዝለቅ አመታትን አስቆጥረዋል።

ይህንንም ተከትሎ በርካታ የቻይና መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያውያን አትሌቶች ዙሪያ በአድናቆት ሰፋ ያለ ሽፋን ይዘው ወጥተዋል።

ቀደም ሲል በቻይና በተካሄዱ ውድድሮች በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፍቃድ ውጭ የመሳተፋቸው ጉዳይ መነጋገሪያ ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል።

በዚሁ ዙሪያ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም አትሌቶቹ ለአበረታች መድሃኒት እንደይጋለጡ ሲል ስጋቱን መግለፁ ይታወሳል።

አትሌቶች ከፌዴሬሽኑ እውቅና ውጭ ሲሳተፉ ከውድድሩ ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም ካለማግኘታቸውም በተጨማሪ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተደጋጋሚ የማራቶን ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ለጤና ችግር እየተጋለጡ መሆኑንም ጠቅሷል።