ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ የዲላ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ገለጹ

72
ዲላ ታህሳስ 14/2011 ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ እንዲቀጥል ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ገለጹ፡፡ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሚገጥሟቸው የአገልግሎት አሰጣጥና ሌሎች ችግሮች ቢኖሩም በሰለጠነ መንገድ ለአስተዳደሩ በማሳወቅ እንዲፈቱ  የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ  ተማሪዎቹ ለኢዜአ  በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡ አሁን  በዩኒቨርሲቲውን ያለውን ሠላማዊ መማር ማስተማር ሂደት ለማስቀጠል ጥረት እንደሚደርጉ አመልክተዋል፡፡ በዩኒቨርስቲው የሁለተኛ ዓመት የእንስሳት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ተማሪ አክሊሉ ቦምቤ እንዳለው የመማር ማስተማር ሂደቱ የተረጋጋና ሰላማዊ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲው ከአምና የተሻለ አገልግሎት አሰጣጥ  እንዳለ ገልፆ የሚያጋጥማቸውን ችግሮች ተማሪዎች በመረጧቸው ተወካዮቻቸው አማካይነት በመጠየቅ እንዲፈቱ እያደረጉ መሆኑን ተናግሯል፡፡ " ወደዚህ ስንመጣ አላማችን መማር ብቻ ነው" ያለው ተማሪ አክሊሉ ትምህርቱ ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ የዩኒቨርሲቲው ሠላም እንዳይናጋ የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡ የአምስተኛ ዓመት የሲቪል ምህንድስና   ተማሪና የሴት ተማሪዎች ህብረት ፕሬዝዳንት ሀያት ሁሴን በበኩሏ በተቋሙ ያለው የመማር ማስተማር ሂደት ሠላማዊ መሆኑን ተናግራለች፡፡ "ይህ ሊሆን የቻለው ችግሮች ባለመኖራቸው ሳይሆን ተማሪው ታጋሽና ቅሬታው እንዲፈታ ሰላማዊ መንገድ የሚከተል በመሆኑ ነው" ብላለች፡፡ ዘንድሮ ትምህርት በጊዜ ቢጀመርም የቤተ መጻሕፍት አገልግሎት በሕንፃ እደሳት ምክንያት ባለመጀመሩ ተቸግረው እንደነበር ጠቅሳ  ከአስተደደር አካላት ጋር በመነጋገር ጊዜያዊ መፍትሄ ማግኘታቸውን አስረድታለች፡፡ አሁን ላይ በተጨባጭ የሚታይ የንፁህ መጠጥ ውሀ ፣ የመጸዳጃ ቤትና የመታጠቢያ ቤት ችግሮች ልዩ ትኩረት የሚሹ መሆናቸውንም ጠቁማለች፡፡ " ዘንድሮ ከሌላው ጊዜ በተለየ የመማር ማስተማሩ በጊዜ መጀመሩ ሙሉ ትኩረታችንን ትምህርታችን ላይ እንድናደርግ አስችሎናል" ያለው ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች የሠላም ፎረም ፕሬዝዳንት ተማሪ ተስፋዬ አያሌው  ነው፡፡ በውጤት ምክንያት ተባረው በድብቅ የሚኖሩ ፣ ለሁከትና ጥፋት መነሳት ከፍተኛ አስተዋፅዖ የሚያበረክቱ ተማሪዎች ከተቋሙ እንዲወጡ መደረጉም የፀጥታ ሥጋት እንዳይኖር የተጫወተው ሚና የላቀ መሆኑን አመልክቷል፡፡ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተመስገን እንግዳ ከተማሪ ሀብረት ፣ከሠላም ፎረም ከሴት ተማሪዎች ህብረትና ሌሎች የተማሪ አደረጃጀቶች ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዳለ አመልክተው ይህን ለማስቀጠል ከተማሪ አደረጃጀቶች ጋር ያላቸውን መልካም ግንኙነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል፡፡ " ለሰላማዊ መማር ማስተማሩ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ የአገልግሎት አሰጣጥና ሌሎች ችግሮችን ለመፈታት ተማሪዎች ሀሳባቸውን በነፃነት የሚገልፁባቸውና ጥያቄዎቻቸውን የሚያቀርቡባቸው በቂ መድረኮችን በመፍጠር  የመፍትሔ እርምጃዎች በመውሰድ ላይ ነን"ብለዋል፡፡ የንፁህ መጠጥ ውሀ፣ የመጸዳጃ  ቤትና  የመዝናኛ ሥፍራዎች እንዲሁም ሌሎች ጉድለቶችም ተማሪዎቹ እንዲስተካከልላቸው መጠየቃቸውንና ደረጃ በደረጃ ለማስተካካል እቅድ አውጥተው እየሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም