የሚገጥማቸውን ችግር በውይይት በመፍታት ለትምህርታቸው እንደሚተጉ የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ገቢ ተማሪዎችን ገለጹ

65
ፍቼ ታህሳስ 14/2011 የሚገጥማቸውን ችግር በውይይት በመፍታት ትምህርታቸውን  በትጋትና በኃላፊነት  መንፈስ ለመከታተል  መዘጋጀታቸውን የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ገቢ  ተማሪዎችን  ገለጹ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከትናንት በስቲያ ጀምሮ  ለሁለተኛ ጊዜ ከተለያዩ የሃገሪቱ  አካባቢዎች ለመጡ 1ሺህ 641  አዲስ  ገቢ ተማሪዎች  ከፍቼ ከተማ ህዝብ ጋር በመሆን  አቀባበል  አድርጎላቸዋል። አዲስ ከመጡት ተማሪዎች መካከል ከአማራ ክልል ደጀን ወረዳ የመጣችው ወጣት ስንዱ አየለ  ሰላም ከምንም ነገር የሚበልጥ በመሆኑ ለዚህና ለትምህርቷ ቅድሚያ ሰጥታ በትጋት እንደምትሰራ ተናግራለች ። በመማር ማስተማር  ሂደት የሚገጥሙ ችግርን  ውይይትን  ብቸኛ አማራጭ  አድርጋ እንደምትጓዝ አስታውቃለች። " ለሰላም ፣ለውይይትና ለአንድነት ዘብ መቆም ያስፈልጋል  " ያለው የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ አስግድ ውለታው  የመቻቻል ባህል በማዳበር  የሚማርበትን  ተቋም  የሰላም ምንጭ  እንዲሆኑ የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግ ገልጿል። ይህንንም ለመጣበት የመማር ዓላማ  በማዋል በጥሩ ሰነ-ምግባር  ትምህርቱን እንደሚቀጥል አመልክቷል። በዩኒቨርሲቲው የኢኮኖሚክስ  ትምህርት ለመከታተል  ከደቡብ ክልል የመጣው ተማሪ አወል ሙሃመድ  በበኩሉ ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ስርዓት  እንዲገነባ የትምህርት ተቋማት ለሰላምና እውቀት ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባል  "ብሏል ። ከማንኛውም አፍራሽ ተግባር  ራሱን በመቆጠብ  ትምህርቱን ብቻ  በትጋት ለመከታተል  እንደወሰነ አስረድቷል። ሁከትና ብጥበጥ  ውድ ጊዜን ከማባከን ውጭ  የሚጠቅመው አምባገነኖችን በመሆኑ ከሰሜታዊነት በመራቅ ለሃገሩ እድገትና ሰላም እንደሚሰራም ተናግሯል ። በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ህብረት ሰብሳቢ ወጣት በላይ አንዳርጌ  አዲስ ገቢ ተማሪዎች  እንግድነት እንዳይሰማቸው የማሰተዋወቅና የማለማመድ ሰራ በህብረቱ እንደሚከናወን አስታውቋል ። ተማሪዎቹ ከአገልግሎት  ሰጪ አካላትና ከሌሎች  የግቢው ማህበረሰብ ጋር  የሚኖራቸው ግንኙነት ስላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል የተማሪዎች አደረጃጀት ፈጥረው እየሰሩ መሆኑን  አመልክቷል። ወጣት በላይ እንዳለው በአሁኑ ወቅትም ወደ ዩኒቨርሲቲው  የመጡ ተማሪዎች በከተማው ሁለት ጣቢያዎች በማቋቋም  ያለ ምንም  መጉላላት ወደ ዋናው ግቢ በዩኒቨርሲቲው ትራንስፖርት  እየደረሱ ነው። ዩኒቨርስቲው  አዲስ ከመሆኑ አንፃር ቅበላው የዘገየው በቂ ዘግጀት በማድረግ ለተማሪዎች የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት  ታልሞ  መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር  ገናናው ጎፌ ናቸው ። ይህም የዘንድሮን የትምህርት ዘመን  ስኬታማ ለማድረግ  በተቻለ አቅም  በግቢው ውስጥ  መሰረተ ልማትን በማሟላት የመማር ማስተማር ሂደቱ የተቀላጠፈ እንዲሆን መደረጉን ገልፀዋል ። በልዩ ልዩ ምክንያት ለነባርና አዲስ ተማሪዎች የባከነው የትምህርት ጊዜ  ለማካካስም ከመምህራንና ተማሪዎች ጋር ስምምነት መደረሱን ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅትም በቅርቡ  በነባር ተማሪዎች መካካል የተፈጠሩ  አለመግባባቶች በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብና በአካባቢው የሃገር ሽማግሌዎች አስታራቂነት መግባባት ተደርሶ ለሁለት ቀናት ተቆርጦ የነበረው ትምህርትም መጀመሩን አስታውቀዋል። በአዲስ ተማሪዎች አቀባበል ስነ -ስርዓቱ  በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አበራ ወርቁ የዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር  ሂደት ሰላማዊና ውጤታማ እንዲሆን  አስተዳደሩ ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል ። የፍቼ ከተማ ወጣቶች ፣ሴቶች ፣የሃገር ሽማግሌዎችና አመራሮች ተማሪዎችን ከመቀበል በተጨማሪ ተሞክሮን መሰረት አድርገው በምሳና ቡና ፕሮግራም ላይ ምክር ሰጥተዋል ። የሰላሌ ዩኒቨርስቲ 1ዐሺህ ተማሪዎችን ማስተናገድ እንዲችል በሶስት ምዕራፍ የተከፈሉ ግንባታዎችን በማከናወን ላይ ያለ ሲሆን በመጪዎቹ አምስት ዓመታትም ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ከሚገቡት 11 አዲስ ዩኒቨርስቲዎች መካከል አንዱ  ነው ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም