ነባር የሰብል ዝርያዎችና እጽዋት ተጠብቀው እንዲቆዩ የተቋቋሙ ባንኮች አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው

71
ዲላ ታህሳስ 14/2011 በደቡብ ክልል እየተመናመኑ የሚገኙ ነባር የሰብል ዝርያዎችና እጽዋት ተጠብቀው እንዲቆዩ  የተቋቋሙ ባንኮች  አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን  የክልሉ አካባቢ ጥበቃና ደን ባለሥልጣን አስታወቀ። ለባለድርሻ አካላት የተዘጋጀ የማህበረሰብ ዘር ባንክና የሰብል ዝርያዎች ጥበቃ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ትላንት በዲላ ከተማ ተካሂዷል ። የባለሥልጣኑ የብዝሀ-ሕይወት ልማትና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት የዕፅዋት ጄኔቲክ ሀብት ባለሙያ ወይዘሮ አለሚቱ ሙሉጌታ እንደገለፁት ስራው  እየተካሄደ ያለው የየአካባቢው ስነ ምህዳርን መሰረት በማደረገ በተቋቋሙ  ስምንት የነባር ሰብል ዘር ባንኮች አማካኝነት ነው ። በባንኮቹ ስር የተደራጁ 13 የነባር ሰብል ዝርያ ጠባቂ ማህበራት መኖራቸውን የገለፁት ባለሙያዋ ማህበራቱ አንድ ሺህ 196 የአባላት እንዳሏቸው ተናግረዋል ። የሰብል ጥበቃው 25 ሄክታር በሚጠጋ የማህበራቱ ማሳና በ279 የአባላቱ የግል ማሳ ላይ የተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል። ባለሙያዋ እንዳሉት  ማህበራቱ ከኢትዮጵያ ብዝሀ-ሕይወት ኢንስቲትዩት ከሚያገኙት የነባር ሰብል ዘር በተጨማሪ በየአካባቢው እየጠፉና እየተመናመኑ የሚገኙ የሰብል ፣  የተለያዩ ዕፅዋትን በማሰባሰብ እና በማሳቸው ላይ በማባዛት ዝርያዎቹ ተጠብቀው እንዲቆዩ አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው፡፡   ጥበቃውን  ለማስፋት የማህበራቱን የማሳ መጠን ለማሳደግ ከየአካባቢው የአስተዳደር አካላት ጋር  በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን አመልክተው "ነባር ሰብሎች የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋሙና ያለግብአት ምርት መስጠት የሚችሉ ናቸው፤ ለምግብ ጣዕማቸውና ማአዛቸው ተወዳጅ ናቸው " ብለዋል፡፡   ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ በማህበራቱ ጥበቃ ከሚደረግላቸው ነባር የሰብል ዝርያዎች መካከል እንሰት፣  በቆሎ፣ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ እና የቅመማ ቅመም ይገኙበታል።   የጌዴኦ ዞን አካበባቢ ጥበቃና ደን ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አክሊሉ በደቻ በበኩላቸው በዞኑ ቡሌ ወረዳ  የሆርሲንሶ የነባር ሰብለ ዘር ባንክ እና የነባር ሰብል ዝርያ ጠባቂ ማህበር  ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡   ማህበሩ በአካባቢው ለመጥፋት ተቃርበው የነበሩ ከምግብነትም ባለፈ ለመድኃኒትነት የሚውሉ ሰብሎችና ዕፅዋትን በመጠበቅ እንዲቆዩና ለትውልድ እንዲተላለፉ በማድረግ አስተዋጽኦ   እያበረከተ እንደሚገኝ ገልፀዋል ፡፡ በ2005 ዓ.ም የተቋቋመው የማህበሩ  ሰብሳቢ   አርሶ አደር ከበደ አዱለ " በማህበሩ አማካይነት ከእጃችን ጠፍተው የነበሩ ሰብሎችን በማሰባሰብ ከ30 በላይ ዝርያዎችን ማቆየት ችለናል" ብለዋል፡፡ አባላቱ ማህበሩ ካለው የዘር ባንክ በብድር ዘር በመውሰድ በማሳቸው ዘርተው እየተጠቀሙ እንደሚገኙ ጠቁመው የአባላቱ ቁጥርም  ሲመሰረት ከነበረው 50 ወደ 118 ከፍ ማለቱን አስረድተዋል፡፡ ፡ የማህበሩ አባል  አርሶ አደር ሰሊ ዶጎማ ከማህበሩ ዘር በብድር በመውሰድ ነባር የሰብል ዝርዎችን በማሳቸው መዝራት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ አሁን ላይ  በራሳቸው ዘር በማቆየት ሶስት ሄክታር በሚሆነው ማሳቸው ላይ ገብስ ፣  ስንዴ ፣ አተር ፣ ባቄላና ሌሎችም ሰብሎችን የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀም እያመረቱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡ የሚያመርቷቸውን ሰብሎች ለምግብ ፍጆታ ከማዋል ባለፈ በአካባቢ ገበያ ለዘር ለሚፈለጉ ገዢዎች በጥሩ ዋጋ እየሸጡ መሆናቸውን አመልክተል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም