ጅማ አባጅፋር በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ከግብጹ አልአህሊ ጋር የመልስ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል

71
አዲስ አበባ ታህሳስ  14/2011 ጅማ አባጅፋር እግር ኳስ ክለብ በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ከግብጹ አልአህሊ ጋር የመልስ ጨዋታውን በአዲስ አበባ ስታዲየም በዛሬው እለት ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ላይ ያደርጋል። የባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊው ጅማ አባጅፋር በ2018 /19 የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ወደ ምድብ ድልድሉ ለመግባት የማጣሪያ ጨዋታውን እያደረገ ይገኛል። ጅማ አባጅፋር በዚህ የማጣሪያ ጨዋታ በመጀመሪያው ዙር ከሜዳው ውጭ ከተጋጣሚው አልአህሊ ጋር ባደረገው ጨዋታ 2 ለ 0 በሆነ ውጤት ተሸንፎ ነው የተመለሰው። በዚህ ጨዋታ ጅማ አባጅፋር ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ በደርሶ መልስ ድምር ውጤት ማሸነፍ ይጠበቅበታል። በደርሶ መልስ ውጤት ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ካልቻለ ደግሞ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ላይ ዝቅ ብሎ የሚወዳደር ይሆናል። ጅማ አባጅፋር የኢትዮጵያን ፕሪሚየር ሊግን የተቀላቀለው ባለፈው ዓመት ሲሆን ሊጉን በተቀላቀለበት ዓመት ሻምፒዮን መሆኑ ይታወሳል። ጅማ አባጅፋር በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ከዚህ ቀደም ምንም አይነት ልምድ የሌለው ሲሆን ተጋጣሚው ከተመሰረተ ከ100 ዓመት በላይ እድሜ ያስቆጠረው የግብጹ አል አህሊ እግር ኳስ ክለብ በሻምፒዮናው በርካታ ታሪክ ያስመዘገበ ነው። በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድርም ስምንት ጊዜ ዋንጫውን በማሸነፍ ከአፍሪካ ክለቦች ሁሉ የተሻለ ታሪክ አለው። በአገሩ ፕሪሚየር ሊግ 40 ጊዜ ዋንጫውን ማንሳት የቻለ ክለብ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም