ባለፉት አምስት ወራት 800 ሰዎች የምህረት አዋጁ ተጠቃሚ ሆኑ

755

ታህሳስ 13/2011 ካለፈው ሃምሌ ወር ጀምሮ ተግባር ላይ በዋለው የምህረት አዋጅ መሰረት  በአምስት ወራት 800 ሰዎች ወንጀላቸው ሙሉ ለሙሉ እንደተሰረዘላቸው የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ።

የጠቅላይ አቃቤ ሕግ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ ለኢዜአ እንደተናገሩት፥ አዋጁ ስራ ላይ ከዋለበት ቀን ጀምሮ በርካታ ግለሰቦች ተጠቃሚ ሆነዋል።

ጥር 13 ቀን 2011 ዓ.ም ቀነ ገደቡ የሚጠናቀቀው አዋጁ ከግንቦት 30 ቀን 2010 ዓ.ም በፊት ለተፈጸሙ ወንጀሎች ይመለከታቸዋል ለተባሉ ግለሰቦች ምህረት ለማድረግ ስራ ላይ መዋሉን ነው የጠቀሱት።

በዚህም መሰረት ጉዳያቸው ተጠርጥሮ ክትትል የሚደረግባቸው፣ ምርመራ የተጀመረባቸው እና ውሳኔ አግኝተው በየማረሚያ ቤቱ የሚገኙ የአዋጁ ተጠቃሚ ሆነዋል ነው ያሉት።

አዋጁ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ታህሳስ 12 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ የወንጀል ክሳቸው በፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ተይዞ የነበሩ 800 ግለሰቦች የምህረት ሰርተፊኬት መውሰዳቸውን ተናግረዋል።

የምህረት ሰርተፊኬት ከተሰጣቸው ውስጥ በኦንላይን ድረ-ገፅ አመልክተው የወሰዱት 71 ብቻ ሲሆኑ አብዛኛዎቹ በአካል እንደወሰዱ ነው የጠቆሙት።

አብዛኞቹ በምህረት አዋጁ የተጀመሩ ክሶችና ምርመራዎች ሙሉ ለሙሉ ተሰርዞላቸው የተለቀቁ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ዝናቡ፥  በማረሚያ ቤት የነበሩ 250 ግለሰቦች ፍርዳቸው ተሰርዞ መውጣታቸውን ነው የጠቆሙት።

በውጭ ሀገር ሆነው በኦንላይን አመልክተው ምህረት የተሰጣቸው 17 ግለሰቦችም እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

አዋጁ ለመከላከያ ሠራዊትና በክልሎች የሚገኙትን እንደሚያካትት ገልጸው ምን ያህል  አመልክተው ምን ያህሉ ተጠቃሚ እንደሆኑ መረጃው እየተጠናቀረ ነው ብለዋል።

የምህረት አዋጁ የማይመለከታቸውም እየተመዘገቡ በመሆኑ ማጣራት በማድረግ ማመልከቻቸው ውድቅ የተደረገባቸው መኖራቸውን አቶ ዝናቡ ገልጸዋል።

አዋጁ ተፈጻሚ የሚሆነው ምህረት ለመስጠት በውስጡ ባካተታቸው ወንጀሎች ውሳኔ ለተላለፈባቸው፣ ተጠርጥረው ለተያዙና ክስ ለተጀመረባቸው ነው ብለዋል።

የምህረት ሰርተፊኬቱን ለመውሰድ በአካል ወይም በማንኛውም አግባብ በኢሜይል፣ በፋክስና ሌሎች ኤሌክትሮኒክ ማመልከቻዎች እያመለከቱ እንዲወስዱ መመቻቸቱንም ጠቅሰዋል።

በዚህም መሰረት የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ባዘጋጀው ድረገፅ እያመለከቱ በተለይ ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የአዋጁ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው ብለዋል።

በምህረት አዋጁ መሰረት ወንጀሉ ተሰርዞለት ነጻ የወጣ ግለሰብ ተመልሶ በዚያው ወንጀል ክስ እንደማይከፈትበት ተናግረዋል።

አቶ ዝናቡ የምህረት አዋጁ የተጀመረውን ለውጥ የበለጠ ለማሳለጥ፣ ከወንጀሉ ነጻ ሆነው በጥሩ ዜጋነት ሀገራቸውንና ህዝባቸውን እንዲያገለግሉ ራሳቸውም የዴሞክራሲ መብቶቻቸውን እንዲተገብሩ ያለመ ነው ብለዋል።

ሀገራዊ አንድነትና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ሲባልም አዋጁ መውጣቱን ጠቁመዋል።

ከሐምሌ 13/2011 ጀምሮ ለስድስት ወር የወጣው የምሀረት አዋጁ የሚመለከታቸው አካላት ሊጠናቀቅ አንድ ወር  የረው በመሆኑ በኦንላይን ወይም በአካል በማመልከት ሰርተፊኬት እንዲወስዱ ጥሪ አድርገዋል።

አዋጁ የተቀጠመለት ቀነ ገደብ ሊራዘም ይችላል ወይስ አይችልም የሚለው ገና አለመታወቁንም አቶ ዝናቡ ጠቁመዋል።