በኦሮሚያ 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር ላይ የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ስራ ይጀመራል

64
አዲስ አበባ ታህሳስ 13/2011 በኦሮሚያ ክልል በቀጣዩ ሳምንት በ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ስራ ይጀመራል። በክልሉ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ በየዓመቱ የሚከናወን ሲሆን በቀጣዩ ሳምንት የሚጀመረው ከእስከዛሬው የተለዩ ተግባራት እንደሚከወኑበት ተነግሯል። የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ ለኢዜአ እንደተናገሩት የዘንድሮው ስራ ቀድሞ የተከናወኑ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራዎችን በመንከባከብ ወደ ተሻለ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በመቀየርና በስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ያተኮረ ይሆናል። የአርብቶና አርሶ አደር አካባቢዎችን ተጨባጭ ሁኔታ ባገናዘብ መልኩ ለመስራት ዝግጅት መጠናቀቁንም ገልጸዋል። የግብርና ባለሙያዎች ስራውን በእውቀትና ክህሎት እንዲመሩ ከክልሉ ሁሉም ወረዳዎች ለተውጣጡ ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱንም ገልጸዋል። ባለፉት ሶስት ዓመታት የተቀዛቀዘውን የኀብረተሰብ ተሳትፎ በማጠናከር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ለማሳደግና በእውቀት ታግዞ ጥራትና ብዛትን ያማከለ ስራ ለመስራት ትኩረት መሰጠቱንም ተናግረዋል። በአርብቶና አርሶ አደሩ ላይ ይታይ የነበረው የግንዛቤ እጥረት በተሰራው ስራ በተገኘው ውጤት አሁን ላይ ጉልበቱን ሳይሰስት በነጻ እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል። እስካሁን በተከናወኑ ተግባራት የአፈር መሸርሸርና መራቆት እንዲሁም የተፋሰሶች የላይኛው አፈር ተጠርጎ መሄድ መቀነሱንና የተራቆቱ ተራሮችም ማገገማቸውን ጠቅሰዋል። በጎርፍ የሚጠቁ አካባቢዎችን መከላከል እንደተቻለ፣ የመኖ፣ ደን ልማትና የውሃ መጠን መጨመር ማሳየታቸውንም እንዲሁ። በሌላ በኩል ቀደም ሲል በተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ከለማ መሬት ውስጥ በ320 ሄክታር ላይ ስራ አጥ ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል። በተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ የተሻለ ተሞክሮ ያላቸውን እያስተዋወቁ መሆኑንና ምስራቅና ምዕራብ ሀረርጌ፣ የሸዋ ዞኖች፣ ምስራቅ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች ምርጥ ተሞክሮ ከተገኘባቸው መካከል ጠቅሰዋል። ከተለያዩ ዞኖች ተውጣጥተው ስልጠና የወሰዱ የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ባለሙያዎችም ከዚህ በፊት በተሰራው ስራ ውጤት ቢገኝም አሁንም ብዙ መስራት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል። አቶ ተስፋዬ ከበደ ከጅማ ዞን እንደተናገረውበጢሮ ሀፈታ ወረዳ በተፋሰስ ልማት የተገኙ ተጨባጭ ውጤቶች  እንዳለና ገበሬው በፊት ከነበረው ኑሮ ሁኔታ እየተለወጠ  መጥቷል፡፡ አክሎም በእርባታ ላይ መሬትን ከንክኪ ውጭ በማድርግ በንብ ማነብ፣ ከብት በማድለብ እና እንዲሁም አትክልትን በመትከል ቡና፣ ፍራፍሬ እንደ አቮካዶና አፕል በመትከል ምርታማነትና ውጤት እየተገኘ ነው። አቶ ብዙአየሁ ምንአለ በበኩሉ በአከባቢያቸው የጎርፍን ቦይ በማውጣት፣ ወንዝ በደለል እንዳይሞላ ፤ አፈር እንዳይሸርሸር እና ብዙ ረግረግ መሬቶች በደለል እንዳይሞላ ፤ ስነ-ምህዳራቸው የተበላሹ መሬቶች ስትራክቸር መሰራታራቱን ተናግሯል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም