የምርጫ ቦርድ ከሚነሳበት የገለልተኝነትና የብቃት ችግር ነጻ የሚያደርደርገው አደረጃጀት ይሰራል-ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ

106
አዲስ አበባ ታህሳስ 13/2011 የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተደጋጋሚ ከሚነሳበት የገለልተኝነትና የብቃት ችግር ነጻ የሚያደርገው አደረጃጀት እንደሚሰራ የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ተናገሩ። በኢትዮጵያ ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) አሸናፊ የሆነባቸው 5 አገር ዓቀፍ ምርጫዎች ተደርገዋል። እነዚህ  ምርጫዎች በአሸናፊው የኢህአዴግ "ነጻና ዴሞክራሲያዊ" እንዲሁም በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ "ፍጹም በማጭበርበር የተሞሉ" ተበለው ሲፈረጁ ቆይተዋል። በተለይ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ለሚሰነዝሩት ወቀሳ እንደምክንያትነት የሚያቀርበው የምርጫ ቦርድ ገለልተኛ አለመሆንን ነው። በቅርቡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ አድርጎ ሲሾም ተቋሙ በገለልተኝነት ሃላፊነቱን እንዲወጣ በማሳሰብም ጭምር እንደነበር ይታወሳል። ወይዘሪት ብርቱካን እንዳሉት፤ ቦርዱ ከገለልተኝነትና የብቃት ችግር ነጻ ሆኖ እንዲያገለግል ከላይ እስከታች አደረጃጀቶችን እየሰራ ነው። በህጋዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ከውጭ ወደ አገር ቤት የተመለሱ ፓርቲዎች እንደፈለጉ ተንቀሳቅሰው አባላቶቻቻውን እንዲመለምሉ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ፓርቲዎች ጋር እየተነጋገሩ መሆኑንም አክለዋል። ቦርዱ የፓርቲዎቹን ጥያቄ ለመመለስ የሚቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ገልጸው፤ ከቦርዱ በተጨማሪ በመንግስት ደረጃም ጉዳዩን በሚመለከት ውይይት እየተካሄደ እንደሆነም ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ እስካሁን ባለው ሂደት በምርጫ ቦርድ ህጋዊ እውቅና ያላቸው ከ70 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሉ ሲሆን፤ እነዚህ ፓርቲዎች ከአንድ ዓመት በኋላ እንደሚካሄድ በሚጠበቀው ስድስተኛው አገር ዓቀፍ ምርጫ ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም