አገር አቀፍ የአሰሪና ሠራተኛ ጉባዔ በቀጣዩ ሳምንት ሊካሄድ ነው

60
አዲስ አበባ  ታህሳስ 12/2011 በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ አገር አቀፍ የአሰሪና ሠራተኛ ጉባዔ በቀጣዩ ሳምንት በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። "የኢንዱስትሪ ሠላም ለአካታችና ዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ሀሳብ ታህሳስ 17 እና 18 ቀን 2011 ዓ. ም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽ ይካሄዳል። የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንዳሉት፤ ጉባዔው በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ያለውን የሰራ ስምሪት ሁኔታ ማየት፣ በወጣቶች የስራ ስምሪትና ዕድሎችንና ተግዳሮቶች፣ በማህበራዊ የምክክርና በነጻ መደራጀት እንዲሁም ለሰላማዊ የኢንዱስትሪ ግንኙነት ያላቸውን ሚና እና ተግዳሮቶች ላይ ምክክር በማድረግ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ ነው። እንዲሁም በአሰሪና ሠራተኛ መካከል ያሉ አለመግባባትን በመፍታት ሠራተኛውን ተጠቃሚ በማድረግ መንግስት የጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማስቀጥል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚደረግ ጠቁመዋል። እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ሰላም እንዲሰፍን፣ የሠራተኛ ደህንነትና ጤንነት እንዲጠበቅ፣ ምቹ የስራ አካባቢዎችና  ስምሪት እንዲስፋፋ የማድረግ ኃላፊነት የሚኒስቴሩ ቢሆንም የሌሎች አካላት ትብብርና ቅንጅታዊ አሰራር የሚጠይቅ ነው። በአሁኑ ወቅት ያለው አደረጃጀትና አሰራር የሰው ኃይል ሊሸከም በሚችል ደረጃ ላይ ባለመሆኑ የዘርፉን ተልዕኮ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ግልጽ በማድረግ ተገቢውን ትኩረት እንዲያኝ የሚካሄድ ጉባዔ እንደሆነም አስረድተዋል። ኢትዮጵያ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ለምታደርገው ኢኮኖሚያዊ ሽግግር የአሰሪና ሠራተኛ ግንኙነት እየሰፋና እየተወሳሰበ የሚሄድ በመሆኑ ከወዲሁ ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግም ዶክተር ኤርጎጌ አብራርተዋል። በጉባዔው ላይ የፌዴራልና ክልል መንግስታት ኃላፊዎች፣ የተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶችና ባለድርሻ አካላትን ጨምሮ አምስት መቶ የሚደርሱ ሰዎች ተሳታፊ እንደሆኑ ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም