በቄለም ወለጋ ዞን 90 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል

82
ጊምቢ ግንቦት17/2010 በቄለም ወለጋ ዞን 90 ሺህ ሄክታር መሬት በመኸር እርሻ በተለያዩ ዘሮች መሸፈኑን የዞኑ ግብርናና ተፍጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። ታርሶ በዘር የተሸፈነው መሬት በዞኑ በመኸሩ ለማልማት ከታቀደው ከ178 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ውስጥ መሆኑን የዞኑ ግብርናና ተፍጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት አስታውቋል። የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ምንተስኖት አለሙ ለኢዜአ እንደተናገሩት በመኸሩ በተለያዩ ሰብሎች ለማልማት ከታቀደው ውስጥ እስካሁን ከ90 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነውን በዘር መሸፈን ተችሏል፡፡ በዞኑ ከተያዘው ግንቦት ወር መጀመሪያ ጀምሮ የተስተካከለ ዝናብ መጣል መጀመሩ የመኸር እርሻውን ከወዲሁ አስቀድሞ ለመጀመር ምክንያት መሆኑም አመልክተዋል። በመኸር አዝመራው ካለፈው ዓመት በግማሽ ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ ያለው ምርት ለመሰብሰብ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት በማጠናቀቅ ወደ ተግባራዊ ሥራ መገባቱንም ምክትል ኃላፊው ተናግረዋል ። ባለፈው ዓመት ከአንድ ሄክታር መሬት በአማካኝ ይገኝ የነበረውን 32 ነጥብ 2 ኩንታል ምርት ዘንድሮ ወደ 34 ነጥብ 4 ኩንታል ከፍ እንዲል በማድረግ 6 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ግብ መያዙንም አመልክተዋል። አቶ ምንተስኖት አንዳሉት ለግቡ መሳካት ከዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ጀምሮ እስከ ቀበሌ ልማት ሠራተኛ ድረስ ለአርሶ አደሩ ግንዛቤና ስልጠና በመስጠት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው። በዘንድሮው  ክረምት የግብርና ሥራ በዞኑ በሚገኙ 11 ወረዳዎች ከ130 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ሲሆን ለትግበራው የሚያስፈልጉ የምርት ማሳደጊያ ግብአቶችም እየቀረበላቸው ነው ተብሏል። በአሁኑ ወቅት  የዝናብ ስርጭቱ የተስተካከለ በመሆኑ አርሶ አደሩ መሬቱን አርሶ በማለስለስ በአሁኑ ወቅት ቦቆሎ፣ ማሽላ፣ ስንዴና ጤፍ እየዘራ ሲሆን ሰሊጥ፣ ኑግና ለውዝ የመሳሰሉ የቅባት ሰብሎች ደግሞ በግንቦት ወር መጨረሻ እንደሚዘሩ አቶ ምንተስኖት አመልክተዋል። በሀዋ ገላን ወረዳ መቻራ ቀበሌ አርሶ አደር መሃሪ ሙሌ በሰጡት አስተያየት የእርሻ መሬታቸውን በማዘጋጀት በግብርና ባለሙያ ምክርና ባገኙት ስልጠና ታግዘው  በቆሎ መዝራታቸውን ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት ከአንድ ሄክታር እስከ 70 ኩንታል የቦቆሎ ምርት ማግኘታቸውን የገለጹት አርሶ አደሩ ዘንድሮም  ሙሉ የግብርና ፓኬጅ ተጠቅመው የተሻለ ምርት ለማግኘት እየተጉ መሆናቸውን አስረድተዋል ። የሞጆ ቀበሌ አርሶ አደር ቀና ደኑ በበኩላቸው የዘንድሮ አየር ሁኔታ ለግብርና ሥራ ምቹ በመሆኑ መሬታቸውን በማለስለስ በቦቆሎና ማሽላ ሰብሎች መሸፈናቸውን ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት በቦቆሎ ከሸፈኑት አራት ሄክታር መሬታቸው ከ300 በላይ ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን የተናገሩት አርሶ አደር ቀና ዘንድሮ ምርታቸውን የበለጠ ለማሳደግ አቅደው እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም