''የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ለሰላም ቁርጠኛ አቋም ካለው ኦነግ ለመነጋገር ዝግጁ ነው'' - የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ

86
አዲስ አበባ ታህሳስ 12/2011 የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን ቁርጠኛ አቋም ካለው ለመነጋገር ዝግጁ ነው ሲሉ የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ተናገሩ። የክልሉን መንግስት እየመራ የሚገኘው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ትናንት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ባሳለፈው ውሳኔ የክልሉን ሰላም እንደሚያረጋግጥ ገልጿል። የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ፥ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ለውጥ የመጣው የኦነግ አባላት፣ የኦሮሞ ህዝብ በተለይም ደግሞ ወጣቱ በከፈለው መስዋእትነት ነው ብሎ እንደሚያምን ገልፀዋል። ለውጡ ወደ ትክክለኛ ዴሞክራሲ እንዲሸጋገር እና ስልጣን የህዝቡ ሆኖ ህዝቡ በምርጫ ተወካዩን እንዲመርጥ እና ህዝባዊ መንግስት እንዲመሰረትም ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ወስዶ እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል። ባለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ መንግስት እና በኦነግ መካከል ጦርነት  እንደነበረ ገልጸው ኢህአዴግ ለውጡን ወደ ራሱ ተቀብሎ መንቀሳቀስ በመጀመሩ ጦርነት ለማቆም ተስማምተናል ብለዋል ። ''የመከላከያ ሰራዊት፣ የደህንነት አገልግሎት፣ የፌደራል ፖሊስ እና የክልል ፖሊሶች ፓርቲን ሲያገለግሉ ነበር ያሉት አቶ ዳውድ፤ ከመንግስት ጋር በተደረሰው ስምምነት የፀጥታ ሀይሉ ገለልተኛ እንዲሆን የመንግስት እንጅ የፓርቲ እንዳይሆን የሚለው ይገኝበታል'' ብለዋል። የኦነግ ሰራዊት በፀጥታ መዋቅር እንዲካተት እና ይህንን የሚሰራ ኮሚቴ እንዲቋቋም ከስምምነት እንደተደረሰም ነው አቶ ዳውድ ኢብሳ የተናገሩት ። በአሁኑ ወቅት ግን ከመንግስት በኩል የተገባው ስምምነት እየተጣሰ ነው ያሉት አቶ ዳውድ፥ በስልጠና ላይ ያሉ የኦነግ ሰራዊት በአመራር አባላት እንዲጎበኙ አለመፍቀድ አንዱ ነው ሲሉ ጠቅሰዋል። አቶ ዳውድ በመግለጫቸው የመከላከያ ሰራዊት የኦነግ ታጣቂዎች ባሉበት አካባቢ መስፈሩ ግጭት እንዲከስት ምክንያት ሆኗል ያሉ ሲሆን፥ ሰሞኑንም በምእራብ ወለጋ በመከላከያ ሀይል እና በኦነግ ታጣቂዎች መካከል ግጭት መፈጠሩንም አንስተዋል። አሁንም መንግስት በክልሉ ሰላም እንዲኖር ቁርጠኛ አቋም ካለው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ከመንግስት ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑንም ነው ሊቀ መንበሩ  የገለጹት። ኦዴፓ የኦሮሞ ህዝብና ወጣቶች የታገሉለትንና እየመጣ ያለውን ለውጥ ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ለመታገል ፓርቲው ከህዝቡ ጋር በመሆን የክልሉን ሰላም እንደሚያረጋግጥ ገልጿል። የጥፋት ኃይሎች በተደራጀ መልኩ የሚሸርቡትን ሴራ በማክሸፍ የህዝቡን ሰላም ለማስጠበቅ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድም አስታውቋል። ኦዴፓ ሰፊውን የኦሮሞ ህዝብ ከጎኑ በማሰለፍ ባካሄደው አዲስ የትግል ስልት ከጨለማ ወደ ብርሃን መሸጋገር የቻለው በጠመንጃ ሳይሆን  ሰላምን በመምረጡ እንደሆነም አስቀምጧል። የፖለቲካ ፉክክር በጠመንጃ አፈሙዝ ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ እንዲሆን በር ተከፍቷል፤ አገርን የዘረፈና የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸመ አካል በህግ እንዲጠየቅም ሰፊ ስራ እየተከናወነ እንደሆነም መግለጹ ይታወቃል። ኦዴፓ የኦሮሞን የፖለቲካ ትግል ለማሻገር ብቻ ሳይሆን ልማት እንዲስፋፋ፣ የኦሮሞ ንብረት ወደ ኢኮኖሚ እንዲለወጥ፣ መሃይምነት እንዲጠፋና የኦሮሞን ህዝብና የወጣቱን ጥያቄ ለመመለስ የተገባውን ቃል ለመፈጸም ይተጋል ብሏል። የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በጥፋት ኃይሎች ወጥመድ በደረሰው ጥቃት ሰላማዊ ዜጎች በፈንጂና በጭካኔ የሽብርተኝነት ድርጊት መሞት፣ የሴቶች መደፈር፣ የንብረት መውደምና የሰዎች እንቅስቃሴ መገታት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘንም ገልጿል። በተቀነባበረ ተንኮል የህግ የበላይነት መጣሱን፣ ህገወጥነት ተስፋፍቶ የህዝቡ እንቅስቃሴ መደናቀፉንና በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያ ትምህርት መቋረጡንና የንግድ እንቅስቃሴ በመቋረጡ ለዜጎች የሚሰሩ ባለሀብቶች የባንክ ብድር መመለስ አቅቷቸው ንብረታቸው በባንክ እየተወረሰ ነውም ብሏል። የመንግስት መስሪያ ቤቶች አገልግሎት እንዳይሰጡ መዝጋት፣ የጦር መሳሪያ መዝረፍ፣ ህግ ባለበት አገር የቢሮ ኃላፊ ማባረር፣ መደብደብ፣ አልፎ አልፎም ጠልፎ መውሰድ፣ ባንክ መዝረፍ ተግባራት እንደሚፈጸሙም ዘርዝሯል። የህግ የበላይነትን ማስከበር የመንግስት ኃላፊነት ነው ያለው የስራ አስፈፃሚው መግለጫ ወንጀል የሚሰሩና ድርጊቱ እንዲፈፀም ሁኔታዎችን የሚያመቻቹ አካላትን ለህግ የማቅረቡን ሥራ በድርጅቱ የሚመራው የክልሉ መንግስት ያስፈፅማል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም