የአየር ንብረት ለውጥ ድርድር ላይ የፓሪሱን ስምምነት ለመተግበር የሚያግዙ ውሳኔዎች ተላልፈዋል..ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ

89
ታህሳስ 12/2011 በ24ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ድርድር ላይ የፓሪሱን ስምምነት ለመተግበር የሚያግዙ ውሳኔዎች መተላለፋቸውን የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ገለጸ፡፡ 24ኛው የአየር ንብርት ድርድር ጉባኤ በፓሪስ ስምምነት ከ2020 ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ በቀረቡ አጀንዳዎች ላይ ድርድር በማድረግ ከተያዘለት ቀነ ገደብ አንድ ቀን በመጨመር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ኢትዮጵያ በመድረኩ የነበራት ተሳትፎ ውጤታማ እንደነበር የአካባቢ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ በነበረው ቆይታ ላይ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ጠቅሰዋል፡፡ የ24ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ድርድር የተጀመረው የባንኮክ ጉባኤ ውጤትና የአጀንዳዎች መድረክ አስተባባሪዎችና የተለያዩ ኮሚቴ ሊቀመንበሮች ለድርድር ባዘጋጁት 236 ገጽ ሰነድና 3 ሺህ ስምምነት ያልተደረሰባቸው ነጥቦች መነሻነት ሲሆን በስብሰባው ላይ  እኤአ ዲሴምበር 15/2018 የፓሪስ የመመሪያ መጽሀፍ 133 ገጽ ያለው ሆኖ ጸድቋል፡፡ በፓሪሱ ስምምነት ከተላለፉ ውሳኔዎች መካከል በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት ቅነሳ፣ የአየር ለውጥ ማጣጣም እንዲሁም ፋይናንስን በተመለከተ ውሳኔ ከተሰጠባቸው ጉዳዮች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ኮሚሽነር ፈቃዱ  ጠቁመዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ያደጉ አገራት ለታዳጊ አገራት የሚያደርጉት የገንዘብ ድጋፍን በተመለከተ ቃል የገቡትን የገንዘብ መጠንና ምንጩን እንዲሁም ለትግበራ የተሰጠውን ድጋፍ በየ2 ዓመቱ ለጽህፈት ቤቱ እንዲያሳውቁ ድንጋጌ አስተላልፏል፡፡ ቴክኖሎጂን በተመለከተ የቴክኖሎጂ አቀራረቦች ለቴክኖሎጂ አካሔድ በየጊዜው የሚደረጉ የዳሰሳ ግምገማ እና የአሰራር ስልቶች ፓሪስ ሩል ቡክ ማእቀፍ ውስጥ ተካቶ የቴክኖሎጂ ድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴዎች  ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ውሳኔ ተቀምጧል፡፡ በተያያዘም የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ የአባል ሀገራት ጉባኤ IPCC የፓሪሱን ስምምነት መሰረት በማድረግ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በመካከለኛው ምእተ ዓመት የአካባቢ የአየር ሙቀት መጠን ከኢንዱስትሪ ዘመን ጋር በማነጻጸር ከ2 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በታች እንዲሆን ልዩ መረጃ እንዲያቀርብ በተጠየቀው መሰረት ከሳምንታት በፊት ውጤቱን ይፋ አድርጎ በጉባኤው የውይይት አጀንዳ በማድረግም ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው አቅጣጫ መመላከቱን ኮሚሽነሩ ጠቅሰዋል፡፡ በ24ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ከ14 ሺህ በላይ የመንግስት ኃላፊዎችና ከፍተኛ ባለሙያዎች፣ከ7ሺህ በላይ የተባበሩት መንግስታት አካላትና ኤጀንሲዎች፣መንግስታዊ ድርጅቶች፣ሲቪል ማህበራት እንዲሁም ከ1500 በላይ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በአጠቃላይ 22ሺህ 500 በላይ ተሳትፈዋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ማእቀፋዊ ስምምነት እኤአ በ1992 የተፈረመ ሲሆን ስምምነቱ አስገዳጅ ሆኖ የገባው እአአ በ1994 መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም