በጅማ ከተማ በመኖሪያ ቤት ላይ የተደረመሰ አፈር የሶስት ሰዎችን ህይወት አጠፋ

87
ጅማ ታህሳስ 12/2011 በጅማ ከተማ  ቦቼ ቦሬ ቀበሌ ውስጥ በመኖሪያ ቤት ላይ የተደረመሰ አፈር ባደረሰው አደጋ የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡ በአደጋው ህይወታቸው ካለፈው ውስጥ የአንድ ቀን አራስ ከነልጇ ይገኙበታል፡፡ የጅማ ከተማ ፖሊስ ጽህፈት ቤት የኮሙዩኒኬሽን ዲቪዚዮን ኃላፊ ኢንስፔክተር ገዛኸኝ አውግቻው ለኢዜአ እንደገለጹት አደጋው የደረሰው አንድ ሲኖትራክ የጭነት ተሽከርካሪ ትናንት ቀን አስር ሰዓት አካባቢ በቦቼ ቦሬ ቀበሌ ቺሻየር በተባለው ሰፈር የደፋው አፈር መኖሪያ ቤት ላይ በመደርመሱ ነው፡፡ መኖሪያ ቤት አፈሩ ከተደፋበት ቦታ በቅርበት ዝቅ ብሎ  የነበረ በመሆኑ ለአደጋው መጋለጡን  አመልክተዋል፡፡ የተደፋው አፈር ተደርምሶ ቤቱ ላይ አርፎ ባደረሰው አደጋም  ከነልጇ ህይወቷ ያለፈው አራስ   የ22 ዓመት ዕድሜ የነበረት መሆኑን  ኢነንስፔክተሩ አመልክተዋል፡፡ የሟቿ ባለቤትም  የአካልና የስነልቦና ጉዳት ደርሶበት በጅማ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገለት እንደሚገኝ ጠቁመው ሶስተኛውም ሟችም ሌላ ህጻን ልጅ  እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ በአደጋው መኖሪያ ቤቱ ከጥቅም ውጪ እንደሆነ ኢንስፔክተሩ አመልክተው አፈሩን የደፋው ሲኖትራኩ አሽከርካሪ ለጊዜው ቢሰወርም ፖለስ ክትትል እያደረገበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም