የጉለሌ ክፍለ ከተማ ያለአግባብ ተይዘዉ የነበሩ የመኖሪያ ቤቶችና የመስሪያ ቦታዎችን ለተጠቃሚዎች አስተላለፈ

አዲስ አበባ 11/2011  በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጉለሌ ክፍለ ከተማ የቤቶች አስተዳደር ጽህፈት ቤት ያለአግባብ ተይዘዉ የነበሩ 120 የመኖሪያ ቤቶችና 64 የመስሪያ ቦታዎችን ለተጠቃሚዎች አስተላለፈ። የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፍስሃ ክፍለ እና የቤቶች አስተዳደር የቁልፍ ርክክብ አድርገዋል። የዕድሉ ተጠቃሚ የሆኑት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ነዋሪዎች፣ የልማት ተነሺዎች፣ የአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ናቸው። ከዕድሉ ተጠቃሚዎች ውስጥ 53 በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ሲሆን፣ 14 የልማት ተነሺዎች፣ 53 የሚሆኑ ደግሞ በልዩ ሁኔታ የቀበሌ ቤት የተፈቀደላቸው ናቸው። 64ቱ ጥቃቅንና አነስተኛ የመስሪያ ቦታዎች ያለአግባብ ተይዘውና ከታለመላቸው አላማ ውጭ ለሌላ አላስፈላጊ አላማ የዋሉ እንደነበር ተገልጿል። በቦታዎቹ ላይ እርምጃ በመውሰድ ከዚህ በፊት ተደራጅተው የመስሪያ ቦታ ላጡ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ኢንተርፕራይዞችና ማህበራት ተላልፏል። ስራ አስፈጻሚው አቶ ፍስሃ ክፍለ ያለንግድ ፈቃድ ተሰማርተው መደበኛ ነጋዴዎችን በመጋፋት እየሰሩ ያሉ ነጋዴዎችን ወደ ህጋዊ መስመር ለማምጣት እና የስራ እድል ለመፍጠር እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል። ክፍለከተማው በቀጣይ የህብረተሰቡን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን ያለአግባብ ተይዘው የሚገኙ ቤቶችንና የስራ ቦታዎች በተገቢው መንገድ ለማከፋፈል የሚሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። የእድሉ ተጠቃሚዎች ክፍለከተማውንና በየደረጃው የሚገኙትን የመንግስት አካላት አመስግነዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም